የሀገር ውስጥ ዜና

የቡና ምርት ለኢትዮ-ቻይና ግንኙነት አስተሳሳሪ ሸቀጥ እየሆነ መጥቷል – አምባሳደር ተፈራ ደርበው

By Yonas Getnet

December 28, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቡና ምርት ለኢትዮ-ቻይና ግንኙነት አስተሳሳሪ ሸቀጥ እየሆነ መጥቷል አሉ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው።

በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው የቻይና-ኢትዮጵያ የቡና ኢኮኖሚና ንግድ ትብብር ኮንፈረንስ በቻይና ሁናን ግዛት ጁጆ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

አምባሳደር ተፈራ ደርበው በመድረኩ ላይ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መጥቷል።

የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለረጅም ዓመታት የዘለቀ መሆኑን በማንሳት አሁን ላይ እየጨመረ የመጣው የቡና ምርት ገበያ ደግሞ አንዱ አስተሳሳሪ ሸቀጥ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ኢፋ ሙለታ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ በማከናወን ላይ የምትገኛቸውን ተግባራት አብራርተዋል።

በግብርና የምርት ሂደት ውስጥ ባሉት የግብዓት፣ ውጤታማ የምርት አሰባሰብ፣ የክምችት እና የሥርጭት መስኮች ዙሪያ በትብብር ለመስራትም ጥሪ አቅርበዋል።

የቡና ምርት በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ከምርትነት ባሻገር ባህላዊ እሴትም ለመሆን ችሏል ያሉት ደግሞ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ናቸው።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ እና ቻይና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ይበልጥ በማጠናከር ረገድ የቡና ምርት ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) የቻይና ገበያ ለኢትዮጵያ ቡና ያለው ፍላጎት እያደገ መምጣቱ ለኢትዮጵያ ትልቅ እድል መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ እና ቻይና በሚያከናውኑት ዘርፈ ብዙ ትብብሮች ውጤታማ ትስስር እንዲፈጠር ከፍተኛ ዝግጁነት እንዳለ አመላክተዋል።

በኮንፈረንሱ ከ700 ሺህ በላይ ሰዎች የሚሳተፉ ሲሆን÷ የኢትዮጵያ ቡናን በቻይና ገበያ የበለጠ ለማስተዋወቅ፣ ገበያ ለመፈለግና ወጪ ንግዱን ለማሳደግ ታልሟል።