አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በፕላን የተሰሩ የገጠር ማዕከላት ለዘላቂ የከተማ ልማት ምሶሶ ናቸው አሉ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ።
የተቀናጀ የገጠር ማዕከላት ልማት የንቅናቄ መድረክ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የተገኙት ሚኒስትሯ በፕላን የተሰሩ የገጠር ማዕከላት ለዘላቂ የከተማ ልማት ምሶሶ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የመንገድ ግንባታን ከገጠር ቤቶች አቅርቦት ጋር በማሳለጥ፣ የባለሙያዎችን አቅም በመገንባትና የተቀናጀ አሰራርን በመፍጠር የገጠር ትራንስፎርሜሽንን ለማፋጠን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
መንግሥት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳው የጎላና ከሰብዓዊ መብቶች መካከል አንዱ የሆነውን የመኖሪያ ቤት በተለይ በከተሞች ተደራሽ ለማድረግ ጥረቶች ሲያደርግ መቆየቱንም አመላክተዋል።
በኢትዮጵያ የገጠር ቤት ጉዳይ በቂ ትኩረት የተሰጠ አለመሆኑን ያነሱት ሚኒስትሯ÷ በመላው ኢትዮጵያ የሚሰሩ መሠረተ ልማት ስራዎች የኢትዮጵያን ብልፅግና ሊያረጋግጡ ይገባል ብለዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተማ ልማትና የኢንዱስትሪ ክላስተር አስተባባሪ ስንታየሁ ወልደሚካኤል የተቀናጀ የገጠር ማዕከላት ልማት ንቅናቄ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ትስስር መፍጠርና የቤት ልማትን ከመንገድ መሠረተ ልማት ጋር ማቆራኘት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በዕውቀትና በክህሎት የበቃ የሰው ኃይል መፍጠርና ቅንጅታዊ አሰራር በማስፋት በዘርፎች መካከል ያለውን ክፍተት መሙላት እንዲሁም በልምድ ልውውጥ ምርጥ ተሞክሮዎችን መቀየርና ማስፋት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ከ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድ ግቦች በገጠር ማዕከላት 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ቤቶችን ለመገንባትና የሚገነቡ ቤቶችም 30 በመቶ ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ መታቀዱ በመድረኩ ላይ ተነስቷል።
በቤዛዊት ከበደ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡- YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.) Facebook https://web.facebook.com/fanasport Facebook WMCC Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!