የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ አምስተኛ ስብሰባውን ታሕሣሥ 13 ቀን 2018 አካሂዷል፡፡
በተሻሻለው የባንኩ የማቋቋሚያ አዋጁ ቁጥር 1359/2025፣ አንቀጽ 23፣ በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሠረት የተቋቋመው የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ በየጊዜው የገንዘብ ፖሊሲዎችን ነድፎ ለባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ምከረ-ሐሳቦችን በማቅረብ፣ ያጸድቃል፡፡ በዚህ ረገድ፣ ኮሚቴው የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት፣ የዋጋ ግሽበት፣ የበጀት፣ የውጭ ኢኮኖሚ፣ የገንዘብ አቅርቦትና የፋይናነስ ዘርፍ አዝማሚያዎች፣ እንቅስቃሴ አመልካቾችን እንዲሁም በሀገር ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ላይ ጉልህ አንደምታ ያላቸው ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ይገመግማል፡፡
ኮሚቴው ከእነዚህ የማክሮ ኢኮኖሚያዊ ግምገማዎችና የቅርብ ጊዜ የወደፊት እይታዎች በመነሣት በቦርዱ ፀድቆ ተግባራዊ የሚደረጉ የፖሊሲ ምክረ-ሐሳቦችን ያቀርባል፡፡
በዚሁ መሠረት ኮሚቴው በውይይቱ ያካተታቸው ዐበይት ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፡-
የዋጋ ግሽበት፡- ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ በመምጣት ህዳር ወር 2018 መጨረሻ ላይ 10.9 በመቶ የደረሰ ቢሆንም የብሔራዊ ባንክ የነጠላ አኃዝ ዓላማ ገና አልተሳካም፡፡ በኮሚቴው ግምገማ ለዋጋ ግሽበት መቀነስ በተከታታይነት ብሔራዊ ባንክ ተግባራዊ እያደረገ ያለው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ፣ የግብርና ምርታማነት መሻሻል እንዲሁም በአስተዳደራዊ ዋጋዎች ላይ እየተወሰደ ያለው ማሻሻያ ቀስ በቀስ መተግበሩ እንደምክንያት ተጠቅሷል፡፡ የዋጋ ግሽበትን ከፋፍለን ስናይ፤ ምግብ-ነክ የዋጋ ግሽበት ህዳር ወር 2018 መጨረሻ 10.6 በመቶ የደረሰ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት 18.6 በመቶ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ፣ ምግብ-ነክ ያልሆነ የዋጋ ግሽበት 11.4 በመቶ የደረሰ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ የታየበት ነው ፡፡ በተመሳሳይ መልኩ፣ ህዳር ወር2018 ወርሃዊ የዋጋ ግሽበት የ1.4 በመቶ ከዜሮ በታች መመዝገቡ የዋጋ ንረት በኢኮኖሚ ላይየሚያሳድረው ጫና እየቀለለ መሄዱን ያመላክታል፡፡
ዕድገትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፡- ኮሚቴው የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ተጠናክሮ እንደቀጠለ እና በ2017 በጀት ዓመትም አጠቃላይ ኢኮኖሚው ባለፉት 8 ዓመታት ከተመዘገበዉ የ7.5 በመቶ አማካይእድገት ከፍ ያለ የ9.2 በመቶ እድገት ማስመዝገብ መቻሉን ተገንዝቧል፡፡ ለዚህም የኢኮኖሚ ዕድገት የአገልግሎት ዘርፍ አስተዋጽኦ በነበረበት በ3.1 በመቶ የቆየ ሲሆን፤ የኢንዱስትሪ ዘርፍ አስተዋጽኦ ደግሞ በ2016 በጀት ዓመት ከነበረበት 2.7 በመቶ ወደ 3.7 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡
ለዚህም ዋና ምክንያት በማዕድን ዘርፍ የታየው ከፍተኛ እድገት ሲሆን በተለይም የወርቅ ምርት አስተዋጽኦ በ2016 በጀት ዓመት ከነበረበት 0.1 በመቶ በ2017 በጀት ዓመት ወደ 1.0 በመቶ ከፍ በማለቱ ነው፡፡ የግብርናው ዘርፍ ለዕድገቱ ያለው አስተዋጾ ደግሞ ከነበረበት የ2.2 የተወሰነ ጭማሪ በማሳየት በ2018 በጀት ዓመት ወደ 2.3 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ የብሔራዊ ባንክ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አመላካቾች (Composite Indicators of Economic Activities) የተጠናከረ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚኖር ያመላከተ ሲሆን ለዚህም በግብርናው ዘርፍ እየታዩ ያሉ ስራዎች፣ ከውጭ ምንዛሬ ለውጡ ጋር ተያይዞ የታዩ መሻሻሎችና መንግስት በብሔራዊ የማኑፋክቸሪንግ ካዉንስል በኩል ለኢንዱስትሪው ዘርፍ በሚያደርገዉ ድጋፍ የምርት ዕድገት መታየቱ፣ እንደ አየር ትራንስፖርት የተጣራ የአገልግሎት ወጪ ንግድ አመርቂ ዕድገት መታየቱ እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፍ የሚጠበቀው ከፍ ያለ እድገት ለኢኮኖሚ ዕድገቱ የራሱን አወንታዊ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይሁንና እንደ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህልና አበባ ያሉ የወጪ ሸቀጦች ላይ፣ ከገቢ ሰቀጦች ደግሞ የጥሬ እቃና የነዳጅ ምርቶች ላይ ከባለፈዉ ዓመት ጋርሲነጻጸር ቅናሽ ታይታል፡፡
የገንዘብ ሁኔታ፡- የገንዘብ ዝውውር አመልካቾች ዘንድ ከፍ ያለ ዕድገት የተስተዋለ ሲሆን ለዚህም በመጠኑም ቢሆን የብድር ዕድገት ጣራው ላላ መደረጉ እንዲሁም የበጀት እና የወጪ ንግድ እድገት መኖሩ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ህዳር ወር 2018 መጨረሻ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚዘዋወረው የጠቅላላ ገንዘብ አቅርቦት (broad money supply) የ38.8 በመቶ፣ መሠረታዊ ገንዘብ (base money) ደግሞ የ67.3 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ሲያሳዩ፣ ሰኔ ወር 2017 መጨረሻ ከነበረዉ ጋር ሲነጻጸርም በቅደም ተከተል የ10.7 እና የ7.8 በመቶ እድገት ታይቷል፡፡ የባንኮች የተከማቸ ብድር ደግሞ 44.5 በመቶ ከፍተኛ ዓመታዊ እድገት ያስመዘገበ ሲሆን በህዳር ወር መጨረሻ ከሰኔ 2017 ጋርም ሲወዳደር የ18.3 በመቶ ጭማሪ አስመዝግቧል፡፡ ለመሰረታዊ ገንዘብ ከፍተኛ እድገት ብሔራዊ ባንክ ከወርቅ ግዢ ጋርበተያያዘ የውጪ ምንዛሪ ክምችት በመጨመሩ እና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ወደ ባንኮች የገባው የጥሬ ገንዘብ መጨመሩ እንደዋነኛ ምክንያት የሚጠቀስ ነው፡፡ ምንም እንኳን መሰረታዊ ገንዘብ ከፍተኛ እድገት ያሳየ ቢሆንም የብድር ዕድገት ገደብ ፖሊሲ በመኖሩ ምክንያት ወደ ጠቅላላ የገንዘብ አቅርቦት የመሸጋገር ሂደት እንዲገታ በማድረጉ፤ የጠቅላላ ገንዘብ ዕድገቱ የተለጠጠ ዕድገት እንዳይመዘገብ ያገዘ ቢሆንም አሁንም ቢሆን የተመዘገበዉ የጠቅላላ ገንዘብ አቅርቦት እድገት ከጠቅላለዉ የሀገር ዉስጥ ምርት እድገት (nominal GDP growth) ከፍ ያለ በመሆኑ በቀጣይ ትኩረት የሚሻ ስለመሆኑ ግንዛቤ ተወስዷል።
የወለድ ተመን ሁኔታ፡- ኮሚቴው የአጭር ጊዜ የወለድ ተመኖች የዕድገት ሁኔታ ጥሩ መሆኑን የተነገዘበ ሲሆን ከማስቀመጫ ወለድ ዉጭ ያሉት ወለዶች ሁሉ ከዜሮ በላይ ሆነዋል፡፡ የ91-ቀናት የመንግስት ግምጃ ቤት ሰነድ የወለድ ምጣኔ ተመን ዓምና ከነበረበት የ14.3 በመቶ ጭማሪ በማሳየት በህዳር ወር2018 መጭረሻ 16.2 በመቶ ሊደርስ ችሏል፡፡ ባንኮች እርስ በእርስ የሚበዳደሩበት የ7-ቀን ቆይታ ያለው አማካኝ የወለድ ምጣኔ ተመን በሚፈለገው የወለድ ምጣኔ ተመን ክልል (Interest Rate Corridor) ውስጥ እንዲቆይ የተደረገ ሲሆን በህዳር ወር መጨረሻ አማካይ ወለዱ 17.3 በመቶ ሆኗል፡፡ በባንኮች መካከል እየተደረገ ያለው የገንዘብ ግብይት ዝውውር ከፍተኛ ዕድገት እያሳየ የመጣ ሲሆን ከጀመረበት ጥቅምት ወር 2017 መጨረሻ እስከ አሁን ብር 1.26 ትሪሊዮን ደርሷል፡፡
የባንክና የፋይናንስ ዘርፍ፡- የባንክ ዘርፉ ዝቅተኛ የተበላሸ ብድር እና በቂ ካፒታል ያለው በመሆኑ ጤናማና የተረጋጋ እንደሆነ በኮሚቴው የተገመገመ ቢሆንም በአንዳንድ ባንኮች ዘንድ በተወሰነ መልኩ የጥሬ ገንዘብ አከል (liquidity) እጥረት መኖሩም ታይቷል፡፡ ይህም በግል ባንኮች ዘንድ በሚታየው ከፍተኛ የብድርና የተቀማጭ ሂሳብ (loan to deposit ratio) ጥምርታ የተንጸባረቀ ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ የጥሬ ገንዘብ አከል ችግሮች አሁን ላይ በባንክ ለባንክ የገንዘብ ገበያና (Interbank Money Market) በብሔራዊ ባንክ ቋሚ የብድር አገልግሎት (Standing Lending Facility) መፍትሔ እያገኙ ይገኛሉ፡፡
የበጀት ሁኔታ፡- ኮሚቴው በበጀት ዓመቱ ጥንቃቄ የተሞላበት የበጀት ፖሊሲ ስርዓት እንደነበር እና ከብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ጋር የተጣጣመ እንደነበር ተገንዝቧል፡፡ ይህም በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አምስት ወራት ለበጀት ጉድለት ማሟያ ከብሔራዊ ባንክ ብድር እንዳይወሰድ ያደረገና የማዕከላዊ ባንኩን የገንዘብ ፖሊሲ አቋም በእጅጉ የሚደግፍ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡ በአንጻሩ የመንግስት ግምጃ ቤት ሰነድ ገበያ ለበጀት ጉድለት ማሟያ እየዋለ ያለበት ሁኔታ ስለተፈጠረ በአምስቱ ወራት ብር 70 ቢሊዮን መሰብሰብ ተችሏል፡፡
የውጭ ኢኮኖሚ ዘርፍ፡- በሐምሌ ወር 2016 ከተወሰደው ሁሉን አቀፍ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ አጠቃላይ የዉጭ ኢኮኖሚ ሚዛን (overall balance of paymnet) ትርፍ ማስመዝገብ የቻለ ሲሆን ይህም የዉጭ ኢኮኖሚ ዘርፉ አሰተማማኝ ሁኔታ ላይ እንዳለ እንደሚያመለክት ኮሚቴዉ ተገንዝቧል፡፡ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አምስት ወራት በሸቀጦች የወጪ ንግድ በተለይም በወርቅና በቡና ከፍተኛ እድገት የታየ ሲሆን በግለሰብ ሀዋላ፣ በተጣራ የአገልግሎት ወጪ ንግድና በካፒታል ሂሳብ አበረታች ዉጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ ይህም ሁኔታ የተንቀሳቃሽ ሂሳብ (current account) እና አጠቃላይ የንግድ ሚዛን (overall balance of payment) በትርፍነት እንዲቀጥሉ በማስቻላቸዉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከምን ግዜም በላይ ከፍተኛ አለምአቀፍ የዉጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ሊይዝ ችሏል፡፡
ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች፡- የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ዕድገት የመቀነስ አዝማሚያ በማሳየት እ.ኤ.አ በ2025 በ 3.2 በመቶ እንዲሁም በ2026 ደግሞ በ3.1 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚኖር የአለም አቀፉ ገንዘብ ተቋም (IMF) መረጃ ያመላክታል፡፡ ይህም ዕድገት በፊት ከተተነበየዉ የ3.3 በመቶ እድገት ጋርሲነጻጸር ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ለዓለም ኢኮኖሚ እድገት መቀነስ እንደ ምክንያት የተጠቀሱት የደወፊቱን በርግጠኝነት የመገመት ችግር (uncertainity)፣ እየጨመሩ የመጡ የንግድ ጦርነቶች ሲሆኑ የታሪፍ ማሻሻያ ጭማሪዉ ግን መጀመሪያ እንደተፈራዉ እንዳልሆነ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ዓለም አቀፍ የዋጋ ግሽበት በተመሳሳይ እየቀነሰ እንደሚሄድ የተተነበየ ሲሆን በ2025 እና በ2026 ወደ 4.2 በመቶ እና 3.7 በመቶ በቅደም ተከተል ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ትንተናና ምክረ-ሀሳቦች
ኮሚቴው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እየወሰደ ያለው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ የዋጋ ግሽበቱን በተከታተይነት የመርገብ አዝማሚያ እንዲኖረው ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ የተገነዘበ ሲሆን የዋጋ ግሽበቱ ወደታሰበዉ የነጠላ አሃዝ ግብ እስኪደርስ ድረስ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲዉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ግንዘቤ ወስዷል፡፡
በመሆኑም ኮሚቴው የሚከተሉትን የገንዘብ ፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን ለቦርድ አቅርቦ አስወስኗል፡፡
አንደኛ፤ ቦርዱ የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተመን (National Bank Rate) አሁን ባለበት 15 በመቶ እንዲቆይ የወሰነ ሲሆን ብሔራዊ ባንክ ለሚሰጣቸው ቋሚ የተቀማጭ ሂሳብ አገልግሎት (standing deposit facility) እና ለቋሚ የብድር አገልግሎት (standing lending facility) የሚከፈሉ የወለድ ተመኖች ባሉበት እንዲቀጥሉ ወስኗል፡፡
ሁለተኛ፤ ኮሚቴው በሶስት ምክንያቶች (1) በህዳር ወር 2018 የባንኮች የብድር ክምቺት በ44.5 በመቶ ከፍተኛ ዓመታዊ እድገት በማስመዝገቡ (2) የብሔራዊ ባንክ የገንዘበብ ፖሊሲ ተመኑ አዲስና ገና ዉጤታማነቱ ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ 3) የባንኮች የጥሬ ገንዘብ አቅም (liqidity) መሸሻል በማሳየቱ አሁን ያለው 24 በመቶ ዓመታዊ የብድር ዕድገት ገደብ እስከ ቀጣዩ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ስብሰባ ጊዜ ድረስ እንዲቆይ ምክረ-ሀሳብ አቅርቦ በቦርዱ ተወስኗል፡፡
ሶስተኛ፤ ባንኮች በመጀመሪያ አምስት ወራት የሰጡት አዲስ ብድር በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ እና በህዳር ወር 2018 የተመዘገበዉ የባንኮች የብድር ክምችት ከፍተኛ መሆኑን ኮሚቴዉ ተገንዝቧል፡፡ ይህም ሁኔታ ጠቅላላ የገንዘብ አቅርቦትን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር እያደረገ በመሆኑ፤ይህ ሁኔታ እንዳይቀጥል ባንኮች በአስገዳጅነት በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡት ሪዘርቭ ምጣኔ (required reserve ratio) ወደ 10 በመቶ ወርያዊ አማካይ ከፍ እንዲደረግ፣ የየእለት መጠባበቂያ ግን በነበረበት 5 በመቶ እንዲቆይ ምክረ-ሀሳብ አቅርቦ በቦርዱ ፀድቋል፡፡ ባንኮች ተግባራዊ ለማድረግ ከሶስት እስከ ስድሰት ወራት ጊዜ ሊሰጣቸዉ ይችላል፡፡
አራተኛ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሀምሌ 2016 ጀምሮ በወለድ ላይ የተመሰረተ የገንዘብ ፖሊሲ ማእቀፍ ተግባራዊ በማድረጉ ትኩረቱ ይህ የፖሊሲ ማዕቀፍ ዉጤታማ ሆኖ ቀጥተኛ ባልሆነ የገንዘብ ፖሊሲ ማለትም በወለድ በኩል በኢኮኖሚ ዉስጥ የሚዘዋወረዉ ገንዘብ ላይ ተጽእኖ በማምጣት ያስቀመጠዉ ዋጋን የማረጋጋት አላማ ማሳካት ነዉ፡፡ በመሆኑም ኮሚቴዉ ብሔራዊ ባንክ የተቀመጠዉ ዝቅተኛ የቁጠባ ወለድ (minimum deposit saving rate) ቁጠባን ለማበረታታትና የባንኩን የፖሊሲ ማእቀፍ የተጣጣመ ለማድረግ የዝቅተኛ ወለድ ተመንን ለገበያዉ እንዲተዉና በአስቀማጮች እና በባንኮች ወይም/እና በሌሎች የገንዘብ ተቋማት መካከል በሚደረግ ድርድር እንዲወሰን ምክረ-ሀሳብ አቅርቦ በቦርዱ ፀድቋል፡፡ በተጨማሪም ብሔራዊ ባንክ የያዘዉ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ አቋም በዋናነት ላስቀመጠዉ ዋጋን የመረጋጋት አላማ ችግር እንደሚገጥመዉ በተገነዘበ ግዜ ያሉትን የፖሊሲ መሳሪያዎች ሁሉ እንደሚጠቀም ያሳዉቃል፡፡
በመጨረሻም ቀጣዩ የኮሚቴው ስብሰባ መጋቢት ወር 2018 መጨረሻ ላይ ወይም እንደ አስፈላጊነቱ ቀደም ብሎ እንዲሆን ተወስኗል፡፡