የሀገር ውስጥ ዜና

ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ብሔራዊ ጥቅምን በማስቀደም የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማብሰር እየሰራ ነው – አቶ አድማሱ ዳምጠው

By Hailemaryam Tegegn

December 30, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ብሔራዊ ጥቅምን በማስቀደም የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማብሰር እየሰራ ነው አሉ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አድማሱ ዳምጠው፡፡

ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።

አቶ አድማሱ ዳምጠው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ብሔራዊ ጥቅምን በማስቀደም የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማብሰር እየሰራ ይገኛል፡፡

ነገን አሻግሮ የሚያይ ትውልድ ለመገንባት ቴክኖሎጂ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፥ መንግስት ካስቀመጣቸው አቅጣጫዎች መካከል አንዱ ቴክኖሎጂ በመሆኑ በዚህ ላይ በትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል።

የሚዲያ ተቋሙ ሀገራዊና ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንዲሁም የኢትዮጵያን የለውጥ ጉዞ የመደገፍ ሚናውን በግንባር ቀደምነት እየተወጣ ይገኛል ነው ያሉት።

የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ተቋማቸው በኢትዮጵያ ጥራት ያለው ስልጠና በመስጠት ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ዘርፉ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን የያዘ በመሆኑ በሰው ኃይል ልማት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ ኢንስቲትዩቱ ከስልጠናና ከምርምር ባሻገር ቴክኖሎጂ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በርካታ ሀገራት ቴክኒክና ሙያን ተጠቅመው ማደግ እንደቻሉ ገልጸው፥ ሰልጣኞች ወደ ሙያ ስልጠና እንዲመጡና የኢንስቲትዩቱን ስራዎች በሚዲያ ለመደገፍ ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽንን ምርጫችን አድርገናል ነው ያሉት፡፡

ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከፍተኛ ተደራሽነት ያለውና ሀገራዊና ማህበራዊ ኃላፊነቱን በሚገባ እየተወጣ የሚገኝ ተቋም መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ