የሀገር ውስጥ ዜና

በፈረንጆቹ 2026 የኢትዮጵያን የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት በስኬት ለመቋጨት ድርድር እየተደረገ ነው

By Hailemaryam Tegegn

December 30, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በፈረንጆቹ 2026 የኢትዮጵያን የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት በስኬት ለመቋጨት ድርድር እየተደረገ ነው አለ የዓለም ንግድ ድርጅት ድርድር ብሄራዊ ኮሚቴ።

ኮሚቴው የኢትዮጵያን የባለብዙ ወገን እና የሁለትዮሽ ድርድሮች ወቅታዊ ክንውን ገምግሟል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትርና ዋና ተደራዳሪ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ሰሞኑን በተካሄደው የዓለም ንግድ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ያደረጉት ተሳትፎ ድርድሩን ወደፊት በመግፋት ያመጣውን አዎንታዊ ውጤት አብራርተዋል።

እስካሁን ከስምንት ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ድርድር መጠናቀቁ አባልነትን ለማሳካት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ተናግረዋል።

ከቀሪ ዘጠኝ አባላት ጋር በፍጥነት ለመቋጨት በትጋት እየተሰራ እንደሚገኝ ነው ሚኒስትሩ ያስረዱት።

በመድረኩ ብሄራዊ ኮሚቴው ከ6ኛው የሥራ ቡድን ስብሰባ በተነሱና በቴክኒክ ኮሚቴው በቀረቡ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳልፏል።

የቴክኒክ ቡድኑ ለ7ኛው የሥራ ቡድን ስብሰባ የሚያስፈልጉ ሰነዶችን አጠናቅቆ ለሴክሬተሪያቱ እንዲያቀርብ አቅጣጫ መቀመጡ ተመላክቷል።

7ኛውን የሥራ ቡድን ስብሰባ በመጪው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት የመጀመሪያ ሳምንታት ውስጥ ለማካሄድ መታቀዱንም ሚኒስትሩ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።

በፈረንጆቹ 2026 የኢትዮጵያን አባልነት በስኬት ለመቋጨት በጠንካራ ተቋማዊ ቅንጅትና ትብብር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

በመላኩ ገድፍ