አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታና ለብሔራዊ መግባባት መሠረት የሚጥልበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል አሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ጠንካራ የሀገረ መንግስት ግንባታን የሚያፋጥኑ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
አካታች ሀገራዊ ምክክር ለማድረግና ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማከናወን ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ሂደትን ማሳካት፣ ምርጫን በተሳካ መንገድ ማካሄድ፣ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታትና የህግ የበላይነትን ማስፈን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የምትሆን ሀገር ለመገንባት ያስችላል ነው ያሉት፡፡
የሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ መሆን የኢትዮጵያን የቆዩ ችግሮች ትርጉም ባለው መልኩ እንደሚፈታ ገልጸው፥ የኢትዮጵያን ስብራቶች ከመጠገን አኳያም ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።
ምክክሩ ሁሉም ዜጎች የተግባቡበት የጋራ ሕገመንግስት እውን ለማድረግና ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ስለሚያግዝ ሁሉም በንቃት ሊሳተፍ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡