የሀገር ውስጥ ዜና

የተባበሩት መንግስታት 3 ነጥብ 45 ቢሊየን ዶላር መደበኛ በጀት አፀደቀ

By Mikias Ayele

December 31, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ለ2026 ስራ ማስፈፀሚያ የሚውል 3 ነጥብ 45 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር መደበኛ በጀት አፀድቋል፡፡

በጀቱ በ193 የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ አባል ሀገራት የፀደቀ ሲሆን የድርጅቱን ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮችን ለማከናወን እንደሚውል ተመላክቷል፡፡

በጀቱ በዋናነት ለሰላም እና ደህንነት፣ ዘላቂ ልማት እና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን ለማስከበር እንደሚውልም ነው የተገለፀው፡፡

በተጨማሪም በጀቱ ለፖለቲካ ጉዳዮች፣ ለዓለም አቀፍ ህግ እና ፍትህ፣ ለቀጣናዊ ትብብር እና ልማት እንዲሁም  ለሰብዓዊ ድጋፎች ማስፈፀሚያ ይውላል ተብሏል፡፡

የጸደቀው በጀት ባለፈው ዓመት ከጸደቀው በጀት አንጻር በሰባት በመቶ ያነሰ ሲሆን፤ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ካቀረቡት ረቂቅ በጀት የ200 ሚሊየን ዶላር ብልጫ እንዳለው ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡

በሚኪያስ አየለ