የሀገር ውስጥ ዜና

ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ እሳቤን በተግባር የገለጠው ስምምነት

By Mikias Ayele

December 31, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመንግስት እና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለአፍሪካ ችግሮች ለአፍሪካዊ መፍትሔ የመስጠት አጀንዳን የሚያጠናክር ነው አሉ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን፡፡

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ ሙሉዓለም ኃይለማርያም ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በአፍሪካ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የውስጥ አቅምን መጠቀም ይገባል።

በተለይም ግጭት እና አለመረጋጋትን ለመፍታት አህጉራዊ ተቋማት ሚናቸውን እንዲወጡ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል ብለዋል።

ለውስጣዊ ችግሮች ውስጣዊ መፍትሔ በመስጠት ከተፅዕኖ ነጻ የሆነ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋም አለመፈጠሩ ግጭቶች በራስ አቅም እንዳይፈቱ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው፤ የተቋማትን አቅም በማጠናከር ለመፍትሔ እንዲሰሩ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአፍሪካ ህብረት ለአፍሪካውያን ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የመስጠት መርህን ወደ ተግባር ለመቀየር በርካታ ጥረቶችን በማድረግ ስኬታማ ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡

ለአብነትም ህብረቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት እንዲቋጭ ማድረጉን እና በሌሎችም ሀገራት የአሸማጋይነት ሚናውን ሲወጣ መቆየቱን አውስተዋል፡፡

በቅርቡ በአማራ ክልል መንግሥት እና በአፋህድ መካከል የተደረሰው ስምምነት አፍሪካዊ መፍትሔ የመስጠት ልምድን የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡

የሰላምና ደህንነት ተመራማሪ ተመስገን ቶማስ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የሚለውን መርሕ ለማጠናክር ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) እና አፍሪካ ህብረት ጋር እየሰራች እንደምትገኝ ገልፀዋል፡፡

በተለይም የአፍሪካ ህብረት ተጠናክሮ የዜጎችን ጥቅም እንዲያስጠብቅ፣ ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር እና በሀገራት መካከል መተማመን እንዲሰፍን ኢትዮጵያ ሚናዋን እየተወጣች ትገኛለች ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከህብረቱ ጋር ትብብር በማድረግ ለሰላም እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ለአብነትም በአማራ ክልል መንግሥት እና አፋህድ መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የሚለውን እሴት በተግባር የገለጠ ነው ብለዋል።

በሚኪያስ አየለ