አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የሀገርን ታላቅነት የሚወስንና ሁሉም በጋራ ጸንቶ የሚቆምለት የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳ ነው አሉ።
የባሕር በር ጥያቄ የወደብ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ትልቅነት የሚወስን ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ ቀደም ባሉት ሥርዓቶች ጥያቄውን የሚያነሱ ሰዎች ጦረኛና ሀገር አተራማሽ አድርጎ የመቁጠር ስህተት እንደነበር ተናግረዋል።
ዛሬም ይህንን የተሳሳተ ትርክት የሚደግሙ አካላት እንዳሉ ጠቅሰው÷ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን በጋራ ብሔራዊ ጥቅማቸው ላይ ጸንተው መቆም ይገባቸዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የመልማት ፍላጎት እንዲሳካ የዜጎች ተሳትፎ መጎልበት እንዳለበትና የሀገሪቷ ሰላምና ደህንነት ይበልጥ መጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት እሴቶች ጎልብተው እንዲወጡና ለሀገር ግንባታ ምሰሶ እንዲሆኑ በትጋት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
የባሕር በር ባለቤትነትን በተመለከተ ኢትዮጵያ የምታነሳው ጥያቄ በቂና አሳማኝ ምክንያቶች ያሉት መሆኑን አብራርተዋል።
ዋና ዋናዎቹም ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊ ምክንያቶች፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሕጋዊ መሠረቶች፣ የጸጥታና የደህንነት ጉዳዮች ጋር የሚገናኙ ናቸው ብለዋል፡፡
በቅርቡ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተደረገው ውይይት የባሕር በር ጥያቄው ሰፊ የሕዝብ መሠረት ያለው መሆኑ መረጋገጡንም ጠቁመዋል።
ጥቂት ታሪካዊ ጠላቶች ካልሆኑ በስተቀር አብዛኛው ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ የጥያቄውን ፍትሃዊነት እየተረዳ መጥቷል ያሉት ተስፋዬ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ በውኃ ሀብቷ እንዳትጠቀምና ከውኃ አካላት እንድትርቅ የተደራጀ ሴራ ሲሰራባት መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮችና በብሔራዊ ጥቅሞች ዙሪያ ሁሉም ዜጎች ወጥ የሆነ አቋም ሊኖራቸው እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።