አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በቀጣይ ሶስት ወራት ውስጥ ለ1 ነጥብ 2 ሚሊየን አርሶ አደሮች የፋይዳ መታወቂያ ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ መሬት አስተዳደር ቢሮ ፡፡
በክልሉ አርሶና አርብቶ አደሮችን የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
የክልሉ መሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰብስቤ ቡናቤ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት ፋይዳ መታወቂያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው፡፡
በክልሉ በቀጣይ 3 ወራት 1 ነጥብ 2 ሚሊየን አርሶ አደሮችን ፋይዳ መታወቂያ እንዲይዙ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ይህም የአርሶ አደሩን የመሬት አስተዳደር መረጃ ሥርዓት ከሌሎች የመረጃ ሥርዓቶች ጋር በማስተሳሰር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግ አመልክተዋል።
የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካትም የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በመድረኩ የፌደራል፣ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡