የሀገር ውስጥ ዜና

ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቅ ጠንካራ የቴክኖሎጂ አቅም ለመገንባት በትኩረት መስራት አለብን – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

By Hailemaryam Tegegn

January 01, 2026

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ ጠንካራ የቴክኖሎጂ አቅም ለመገንባት በትኩረት መስራት አለብን አሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የምርምርና ልማት ፖሊሲ ምረቃና የማዕከል ምስረታ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የአንድን ሀገር ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አቅም በመገንባት የማድረግና የመፈፀም ችሎታን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ጥናትና ምርምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡

ከተቋም አልፎ ለሀገራችንና ለአፍሪካ ሁለንተናዊ ዕድገት አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ የምርምር ስራዎችን በመስራትና በማዳበር አዳዲስ ግኝቶችን ልናበለፅግ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ችግር ፈቺና የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ ጠንካራ የቴክኖሎጂ አቅሞችን በመፍጠር ዘመን ተሻጋሪ የልማትና የምርምር ሥራዎችን በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የማዕከሉን መመስረት በማብሰር ምስረታው ዕውን እንዲሆን አስተዋፅኦ ላበረከቱ አመራሮች፣ ሙያተኞችና ክፍሎች ዕውቅና መስጠታቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡