ቢዝነስ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘቡ ከ2 ትሪሊየን ብር በላይ ደረሰ

By sosina alemayehu

January 01, 2026

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ ከ2 ትሪሊየን ብር በላይ ደረሰ።

ባንኩ በ2025/26 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ብቻ ከ325 ቢሊየን ብር በላይ ተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰቡንና አጠቃላይ ተቀማጩም 2 ትሪሊየን ብር መድረሱን የባንኩ ማኔጅመንት አባላት በተገኙበት አስታውቋል።

የባንኩ ፕሬዚዳንት ተወካይና የኮርፖሬት አገልግሎቶች ም/ፕሬዚዳንት ኤፍሬም መኩሪያ ንግድ ባንክ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አጠቃላይ ተቀማጭ ብር በእጥፍ ማሳደጉን ተናግረዋል።

አፈጻጸሙም ለባንኩ ትልቅ ስኬት እንደሆነና የ2030 የባንኩ ስትራቴጂ ውጤት መሆኑን አንስተዋል።

በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 750 ቢሊየን ብር ተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ ለማሰባሰብ ታልሞ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የባንኩ የቢዝነስ ተቀዳሚ ም/ፕሬዚዳንት ደረጀ ፉፋ በበኩላቸው÷ ከባንኩ ሪጅኖች እስከ ቅርንጫፍ ድረስ ለባንኩ ውጤታማ አፈጻጸም በርካታ ውጣ ውረዶች መታለፋቸውን አስረድተዋል።

ኃላፊዎቹ ለስኬቱ መገኘት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ለነበራቸው ሪጅኖች፣ ዲቪዥኖች፣ ዲስትሪክቶች እንዲሁም ሠራተኞችና ደንበኞች ምስጋና አቅርበዋል።