አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲሱ የጉምሩክ መመሪያ ግልፅነትና ተዓማኒነት ያለው የሸቀጦች ዋጋ አተማመን እንዲኖር ያስችላል አሉ የጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ፡፡
የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በአዲሱ የጉምሩክ ዋጋ አተማመን መመሪያ ዙሪያ ከፍተኛ የህግ ተገዥነት ካላቸው አስመጪዎች፣ አምራቾችና የጉምሩክ አስተላላፊዎች ጋር ውይይት እያካሄደ ነው፡፡
ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ በኢትዮጵያ አምራች ዘርፉን ለማበረታታት መንግስት የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል፡፡
በአዲሱ መመሪያ መሰረት ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልበት ከጉምሩክ ቁጥጥር የተለቀቀ ወይም የተሟላ የጉምሩክ ስነስርዓት ያልተፈፀመበት ዕቃ ሆኖ ቀረጥና ታክስ ለማስከፈል አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ዋጋ አተማመን ተፈጻሚ እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም የጉምሩክ ስነስርዓት ተፈጽሞበት በተለቀቀ ዕቃ ላይ የድህረ ዕቃ አወጣጥ ኦዲት ሲከናወንና ከንግድ ዓላማ ውጪ ወደ ሀገር በሚገባ ወይም በጊዜያዊነት ወደ ሀገር የሚገባ ዕቃ ዋጋ አተማመን ላይ መመሪያው ተፈጻሚ እንደሚሆን ነው የገለጹት፡፡
በኮሚሽኑ ፀድቆ ተግባራዊ የሆነው መመሪያ ቁጥር 1080/2017 ፍትሃዊና ተዓማኒነት ያለው የጉምሩክ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ አሰራሮችን ለመተግበር ያግዛል ብለዋል፡፡
በግዛቸው ግርማዬ