አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የወንጀል መከላከልና ምርመራ ሥራን ወደ ላቀ የቴክኖሎጂ ምዕራፍ በሚያሸጋግር መልኩ ይተገበራል አሉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ቁልፍ ትልሞች ተደራሽነትን ማስፋት፣ እኩል ዕድል መፍጠር፣ በዜጎችና ተቋማት መካከል መተማመንን ማጎልበት መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወቃል።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በፖሊስ ሥራዎች ላይ ለውጥ እንዲመዘገብ ማስቻሉን አስታውሰዋል።
ሕብረተሰቡ የወንጀል ጥቆማዎችንና የሚፈልጋቸውን መረጃዎች በአካል ፖሊስ ጣቢያ ሳይገኝ በሞባይል ስልኩ ብቻ የሚያገኝበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ኮሚሽነር ጄኔራሉ ገልጸዋል።
ከአንድ ወር በኋላ ሰው አልባ ፖሊስ ጣቢያ በአዲስ አበባ ሥራ እንደሚጀምር መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የጣት አሻራን አውቶሜት የማድረግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ የጦር መሣሪያ ምዝገባን ከፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ጋር በማስተሳሰር ቁጥጥር የሚደረግበት ሥርዓት መዘርጋቱንም ጠቅሰዋል።
ፌደራል ፖሊስ በ2030 የወንጀል ምርመራ፣ መከላከልና የውስጥ አሠራሮችን በቴክኖሎጂ ሙሉ በሙሉ ለማዘመን በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ፖሊሳዊ አገልግሎቶችን በላቀ ደረጃ የሚያጎለብት መሆኑን አስረድተዋል።
በቀጣይም 196 ሀገራት የሚሳተፉበት የዓለም አቀፉ ፖሊስ (ኢንተርፖል) ጉባኤ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ጠቁመው፤ ተቋሙ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና የዘመነ መሆኑን ለማሳየት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለወንጀል መከላከልና ምርመራ ሥራዎች ቴክኖሎጂን በስፋት እየተጠቀመ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የተለያዩ መተግበሪያዎችን በራስ አቅም በማበልጸግ እንዲሁም ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር በመተባበር ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።