አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ላጋጠማቸው 177 ሕጻናት የዊልቼር ድጋፍ አድርገዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷አዲስ አበባን በአፍሪካ ደረጃ ሕጻናትን ለማሳደግ ምቹና ተመራጭ ከተማ እንድትሆን የተጀመረው ሥራ ፍሬ እያፈራ ይገኛል።
በከተማ አስተዳደሩ እየተተገበረ ባለው የቀዳማይ ልጅነት ልማት መርሐ ግብር አማካኝነት ውስብስብና ከፍተኛ የአካል ጉዳት ላለባቸው 177 ሕጻናት ምቹ የዊልቸር ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
ዊልቸሮቹ እንደ ሕጻናቱ የአካል ጉዳት ሁኔታ ተስማሚ ሆነው መሠራታቸው ለሕጻናቱ ምቹና ውጤታማ ድጋፍ ይሰጣሉ ነው ያሉት፡፡
ድጋፉ የአካታችና ሁሉን አቀፍ ልማት አካል መሆኑን ጠቁመው ÷ መዲናዋ ማሕበራዊ ፍትሕ የነገሰባት ትሆን ዘንድ በቀጣይ ተደራሽ ያልሆኑ ሕጻናትን ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በጎ ተግባሩን ላስተባበሩና በቅንጅት ለሰሩ ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡