አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በተያዘው በጀት ዓመት 500 ሺህ ስማርት የቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎችን ለመግጠም ታቅዶ እየተሰራ ነው አለ።
በአገልግሎቱ የሪቨኑ ፕሮቴክሽን እና ዩኒፋይድ ፕሪፔይመንት ፕሮጀክት ኃላፊ ለምለም ባሳዝነው÷ ስማርት የቅድመ ክፍያ ቆጣሪ ደንበኞች ካሉበት ሆነው ስልካቸውን ተጠቅመው ኃይል መግዛትና አጠቃቀማቸውን ለመከታተል ያስችላል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ከክፍያ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎችን ይፈታል ነው ያሉት ፡፡
እስካሁንም በአዲስ አበባ ከተማ ለ6 ሺህ 500 ነባር እና 3 ሺህ 500 አዳዲስ ደንበኞች ስማርት የቅድመ ክፍያ ቆጣሪ መገጠሙን ጠቅሰዋል፡
ቆጣሪዎቹ የተገጠሙት በገርጂ 40/60፣ ባልደራስ ኮንዶሚኒየም፣ መካኒሳ እና ሃና ፉሪን ጨምሮ በሌሎች የጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ነው ብለዋል፡፡
125 ሺህ ባለ ሶስት ፌዝ እና 375 ሺህ ነጠላ ፌዝ በአጠቃላይ 500 ሺህ ስማርት የቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎች ወደ ሀገር መግባታቸውን ገልጸው÷ ቆጣሪዎቹ በተያዘው በጀት ዓመት ይገጠማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ብዙ ለውጥ የሚያመጣውን ስማርት የቅድመ ክፍያ ቆጣሪ ለማስፋፋት ተጨማሪ 120 ሺህ ቆጣሪዎች ወደ ሀገር ለማስገባት መታዘዙን ጠቁመዋል።
በመሳፍንት እያዩ