አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከቁልፍ የቦንድ ባለቤቶች ኮሚቴ ጋር ከ1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የቦንድ ዕዳ ሽግሽግ ለማድረግ በመርህ ደረጃ ከስምምነት ደርሳለች፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው÷ ከፈረንጆቹ ታሕሣሥ 23 ቀን 2025 እስከ ጥር 1 ቀን 2026 ባለው ጊዜ ውስጥ የአንድ ቢሊየን ዶላር ቦንድ ዕዳን ለማዋቀር ከቁልፍ የቦንድ ባለቤቶች ኮሚቴ ጋር ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱም ኢትዮጵያ ከቦንድ ባለቤቶች ኮሚቴ ጋር የቦንድ ብድር ሽግሽግ ለማድረግ በፋይናንስ መርህ ደረጃ ከስምምነት ላይ ደርሳለች፡፡
ስምምነቱ ኢትዮጵያ ከአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ጋር ካላት የብድር ፕሮግራም ጋር የሚስማማ እና በኢትዮጵያ ይፋዊ የአበዳሪዎች ኮሚቴ (ኦሲሲ) የኢትዮጵያን ዘላቂ የብድር ሽግሽግ በሚያስተካክል መልኩ ግምገማ የተደረገበት መሆኑ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም በነበረው ውይይት ከኮሚቴው ጋር ከፋይናንስ ነክ ውጭ ባሉ ጉዳዮች እንዲሁም የብድር ሽግሽግን በተመለከተ የሚወጡ አዳዲስ ማዕቀፎችን በተመለከት በትብብር ለመስራት ከስምምነት ላይ መደረሱ ተመላክቷል፡፡
ሚኒስቴሩ ኮሚቴው እና የኮሚቴው አማካሪዎች በውይይቱ ወቅት ላሳዩት ትብብር እና ቀናኢነት ምስጋና አቅርቧል፡፡
በሚኪያስ አየለ