አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ቀኑ አጭር ሌሊቱ ደግሞ ረጅም የሚባለው የገና ጀምበር የመሬት ሽክርክሪት ዑደት የሚፈጥረው እንደሆነ በዘርፉ የተሰማሩ የሥነ ፈለክ ሊቃውንት ያስረዳሉ።
መሬት በራሷ ዛቢያና በፀሐይ ዙሪያ መሽከርከሯ ለቀንና ሌሊት መፈራረቅ እንዲሁም ለወቅቶች መለያየት መንስዔ ሲሆን÷ የመሬት 23 ነጥብ 5 ዲግሪ ዘምበል ማለትም አንዱ የልዩነቶች መንስዔ መሆኑ ይገለፃል።
በዓለማችን የሰዓት አቆጣጠር፣ የክረምትና በጋ፣ ፀደይና መፀው ልዩነቶች የሚታዩትም በዚህ ምክንት እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ያመላክታሉ።
መጋቢትና መስከረም ሌሊቱም ቀኑም እኩል ነው፤ ጥቅምት ላይ ደግሞ ቀኑ 11 ሰዓት ሲሆን ሌሊቱ 13 ሰዓት ይሆናል። ሕዳር ወር ሲገባ ደግሞ ቀኑ 10 ሌሊቱ 14 ሰዓት እንደሚሆን በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ። ታሕሣሥ ወር ላይ ደግሞ ቀኑ 9 ሌሊቱ 15 ሰዓት ይሆንና ከጥር ወር ጀምሮ ባሉት ወራት ቀኑና ሌሊቱ መስተካከል ይጀምራል።
ወራቶች በጊዜ ዑደታቸው የቀንና ሌሊት መርዘም አንዳንዴም እኩል መሆንን ተፈራርቀው እየተቀበሉ ዓመትን ይጓዛሉ። ወርሃ ታሕሣሥ ግን የወሩን ስያሜ ለገና በመስጠት የገና ጀምበር እየተባለ ሲጠራ ይደመጣል።
የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ መምህርና የሀገር በቀል ዕውቀቶች ተመራማሪ ጌትነት ፈለቀ (ዶ/ር) የገና ጀምበር ስንል ታሕሣሥ ላይ ፀሐይ ቶሎ ትጠልቃለች ወይም ቀኑ ረጅም አይደለም የሚል ቀጥተኛ ትርጉም እንዳለው ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል።
ይህም የሚሆነው መሬት ዘምበል በማለት 23 ነጥብ 5 ዲግሪ ላይ በመሆኗ ወቅቶችን እንዲሁም ቀንና ሌሊቱን እንዲቀያየር እንደሚያደርግ አንስተዋል።
አሁን ላይ የመሬቷ ደቡቡ ክፍል ወደ ፀሐይ ማጋደሉን ተከትሎ ይህ አካባቢ ረጅም ፀሐይ እንደሚያገኝና በሰሜኑ ክፍል ደግሞ ቀኑ እያጠረ ጨለማው እየረዘመ እንደሚሄድ አስረድተዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ ከምድር ወገብ ሰሜናዊ ክፍል ላይ ስላለች ቀኑ እንደሚያጥር ያሳያል ነው ያሉት።
በመጽሐፈ ሔኖክ፣ ስንክሳር እና ባሕረ ሐሳብ በመሳሰሉ የኢትዮጵያ መጽሐፍት ላይ ወቅቶቹን በተመለከተ የተዘጋጁ ጽሑፎች መኖራቸውን የገለጹት ጌትነት (ዶ/ር)÷ በዚህም ቀኑ ከ9 ሰዓት እንደማይወርድና ሌሊቱ ደግሞ ከ15 ሰዓት እንደማይበልጥ ተጽፎ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ ሙሉ የታሕሣሥ ወር ቀናት ተመሳሳይ ሰዓት እንደማይጋሩና የዘንድሮ ታሕሣሥ 12 ቀን የቀኑ ርዝመት 11 ሰዓት ከ36 ደቂቃ እንዳለው መመዝገቡን ገልጸው÷ ይህም በዓይን ብቻ አይተን መለየት የምንችለው ባለመሆኑ ፀሐይ ስትገባና ስትወጣ በመለካት ማወቅ እንደሚቻል አመላክተዋል።
በአድማሱ አራጋው