አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከነባሩ የሃሳብ አጥር በመውጣት የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በጋራ እንስራ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን አስመልክተው “የምሁራን ሚና ለሀገራዊ ብልጽግና” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡
በጽሑፋቸውም ለሀገር እድገት የግል ዘርፍን ጉድለት የሚሞላ፣ ሃሳብ የሚገዛ፣ ጠንካራ የመምራትና የመመልከት አቅም ያለው መንግሥት አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።
ስኬትንና ተግዳሮትን የሚካፈል የግል ሴክተር እንዲሁም የሚያስተሳስር ችሎታን ወደ መሰረተ ልማት የሚቀይርና የሚገነባ መካነ ትምህርት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።
ማሕበረሰቡ ደግሞ በሒደትም ሆነ በውጤት ባለቤት የሆነ ፤ ያሉ ፈተናዎችንና ድሎችን የሚቋደስ ሕዝብ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ለዚህም ብዝሃ ዘርፋዊ አሰራር ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ኢንተርፕርነር የሆነ እሴት መፍጠር የሚችል የግል ዘርፍ ሊኖር ይገባል ብለዋል።
እንዲሁም አስቻይ ሥርዓት እና መዋቅር ያለው ኢንተርፕርነር መንግሥት እና ሃሳብ መፍጠር የሚችል ኢንተርፕርነር ምሁራዊ ሚና ሊኖር ይገባል ነው ያሉት።
መዋቅራዊ ችግሮች የሚፈቱት እነዚህ ተዋንያን ተሰናስለው ሥራቸውን ሲሰሩ እንዲሁም የተሻገረና የተሳሰረ ምሁራዊ ሚና ሲታከልበት መሆኑን ጠቁመው ÷ በአንድ ወገን ጥረትና ሥራ የተሟላ ውጤት ሊመጣ እንደማይችል ጠቅሰዋል።
ምሁራዊ ሚናን እንዴት እንወጣ ለሚለውም በእያንዳንዱ የሃሳብ ገበያ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ፣ ከራስ የተሻገረ አላማ መያዝና ሃሳብ ትልቁ ግብዓት መሆኑን በማመን ድልድይ በመሆን መስራት ሲቻል እንደሆነ አስረድተዋል ።
ሃሳብን ከሃሳባዊ እይታ ባሻገር፣ ምሁርነትን ደግሞ ከሙያዊ ስኬት ባሻገር እንዲሁም ክፍል ከጊዜ ሰሌዳ ባሻገር መሆኑን እያሰቡ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
ችግርን ከመተንተን እና ጉድለትን ከማሳየት ባሻገር ላለው ችግር መፍትሄ ማምጣት መቻል እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከነባሩ የሃሳብ አጥር በመውጣት የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በጋራ እንስራ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሶስና አለማየሁ