የሀገር ውስጥ ዜና

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገና በዓልን በማስመልከት ለ300 ሺህ ነዋሪዎች ማዕድ አጋራ

By Hailemaryam Tegegn

January 05, 2026

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መጪውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ከ300 ሺህ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች ማዕድ አጋርቷል፡፡

በከተማዋ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ምንም የገቢ ምንጭ ለሌላቸው፣ ለማህበራዊ ችግር ለተጋለጡ፣ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸውና አቅመ ደካማ ወገኖች የማዕድ ማጋራት መርሐግብር ተካሂዷል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የፍቅር መገለጫ በመሆኑ የማዕድ ማጋራቱ ለተቸገሩ ወገኖቻችን ያለንን ፍቅር በተግባር የምንገልጽበት ነው ብለዋል።

መርሐ ግብሩ ጊዜያዊ ችግርን ለማለፍ እጅ ለአጅ ተያይዘን የምንቆምና ለዘላቂ ልማት የምንተጋ ታላቅ ሕዝቦች መሆናችንን በተግባር ያረጋገጥንበት ነው ያሉት ከንቲባዋ፥ ጥልቅ የመረዳዳትና የአብሮነት እሴትን የሚያጸና የበጎነት ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሁሉም በዓላት ካላቸው ላይ ለወገኖቻቸው በማካፈል ለዚህ በጎ ተግባር መሳካት አብረው ለቆሙ ልበቀና ባለሀብቶች እንዲሁም በትጋት ላስተባበሩ ወጣቶችና አመራሮችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡