የሀገር ውስጥ ዜና

ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን አጥተው የነበሩ ወንዞች ታክመው ሲያንሰራሩ ማየት ትልቅ ስኬት ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By Mikias Ayele

January 09, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን አጥተው የነበሩ ወንዞች ታክመው ሲያንሰራሩ ማየት ትልቅ ስኬት ነው አሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡

ከንቲባዋ በመዲናዋ እየተገነቡ የሚገኙትን የቀበና እና የጊንፍሌ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶችን የሥራ ሂደት ገምግመዋል።

ምልከታውን አስመልከቶ ከንቲባዋ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የወንዝ ዳርቻ ልማት ለሀገራችን አዲስ ተሞክሮ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ አስደናቂና ለውጥ አምጭ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

ብክለት ተወግዶ፣ የአፈርና የሥነ-ምህዳር ጥበቃ ተደርጎላቸው፣ ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን አጥተው የነበሩ ወንዞች ታክመው ሲያንሰራሩ ማየት ትልቅ ስኬት መሆኑን አንስተዋል፡፡

በተለይም 19 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውና ከእንጦጦ እስከ ካራማራ ድልድይ ድረስ የሚዘልቀው የቀበና ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት ግንባታው ወደ መጠናቀቅ መቃረቡን ጠቁመዋል።

የደረቁ የውሃ ምንጮች እንደገና መፍለቃቸውንና፣ መጥፎ ሽታ ተወግዶ አካባቢው በሀገር በቀል ዛፎች ተከቦ ለነዋሪዎች ምቹ፣ ጤናማና ንጹሕ አየር የሚተነፈስበት ማራኪ ገጽታ መላበሱን ተናግረዋል፡፡

የመዲናዋን ዘላቂ ልማት የሚያረጋግጡ የውሃ ግድቦች፣ ድልድዮች፣ ዘመናዊ የእግረኛና የሳይክል መንገዶችና የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ጨምሮ ሰፋፊ የልማት ስራዎች መከናወናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

የከተማችንን ገጽታ የሚቀይሩ የአረንጓዴና የውበት ሥራዎችም በመጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡

እነዚህ የልማት ሥራዎች በአሁኑ ወቅት ለሪል እስቴትና ለሆቴል አልሚዎች እጅግ አዋጭ የኢንቨስትመንት አካባቢ ፈጥሯል ያሉት ከንቲባዋ÷ ዕውቀትና ገንዘብ ያላቸው ባለሀብቶች በዚህ ልዩ የልማት ዕድል ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከንቲባዋ በመልዕክታቸው ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ እየሰሩ ያሉ አመራሮችን፣ባለሙያዎችን፣ ኢንተርፕራይዞችንና የአካባቢውን ነዋሪዎች አመስግነዋል፡፡