አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ለኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ስርዓት የዘመናት ስብራት ምላሽ የሚሰጥ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት÷ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት 80 ዓመታት የጥንታዊ ሀገር ምልክትና ኩራት ሆኖ ስኬታማ ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል።
አየር መንገዱ በእነዚህ ዓመታት ያለፈባቸው መንገዶች አልጋ በአልጋ እንዳልነበሩ አስታውሰው÷ በኢትዮጵያ ያጋጠሙ የመንግሥት ስርዓት መለዋወጥም ሆነ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሳይበግሩት በከፍተኛ ብቃት የአፍሪካ ኩራት መሆን መቻሉን አብራርተዋል።
ከአየር መንገዱ የስኬታማነት ጉዞ ጀርባ ያለው ታላቅ ምስጢር ደግሞ ጠንካራ የኮርፖሬት ባህል መገንባት መቻሉ እንደሆነም አንስተዋል።
በዚህም አየር መንገዱ ጥቅሙን ባስጠበቀ መልኩ ያለምንም ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆኖ በዓለም አቀፍ የቢዝነስ ህግ እየተመራ መቀጠሉን ነው የተናገሩት።
ለደሕንነት ቅድሚያ የሚሰጥ፣ በፈጠራና ትጋት የሚሰሩ አመራሮች፣ በተደመረ አቅም የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በትጋትና ኃላፊነት የሚሸከሙ ሰራተኞች ያሉት መሆኑንም አመልክተዋል።
ተቋሙ ዘወትር ለመማር ዝግጁ መሆኑ ደግሞ አየር መንገዱን ልዩ እንደሚያደርገው አብራርተዋል።
ዛሬ ግንባታው የተጀመረው የአውሮፕላን ማረፊያው በዓመት 110 ሚሊየን መንገደኞችን በማስተናገድ በዓለም ላይ ካሉ ጥቂት ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያዎች አንዱ እንደሚሆን ተናግረዋል።
አዲስ የሚገነባውን አውሮፕላን ማረፊያ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጋር የሚያገናኝና በአንድ ጊዜ 12 ተሽከርካሪ ማስተናገድ የሚችል የፍጥነት መንገድ እንዲሁም ፈጣን የባቡር መንገድ እንደሚገነባ ገልጸዋል።
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በሰማይ ለሚበሩ መርከቦቻችን እንደ ትልቅ ወደብ ሆኖ ያገለግላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይህም ለኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ስርዓት የዘመናት ስብራት ምላሽ የሚሰጥ ስለመሆኑ መግለፃቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በርካታ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ስኬታማ እንደሆነ ሁሉ የሚገጥሙን ፈተናዎች ይበልጥ እንድንተጋና ለስኬታችን እንድንጸና ያደርጉናል ሲሉም ተናግረዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ በሁለት ምዕራፍ የሚከናወን ሲሆን÷ ግንባታው ሲጠናቀቅ በዓመት 110 ሚሊየን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ሲጠናቀቅ 60 ሚሊየን መንገደኞች የማስተናገድ አቅም በመያዝ በፈረንጆቹ 2030 እንደሚጠናቀቅም ነው የተገለጸው።