የሀገር ውስጥ ዜና

የ“ሴራ” በዓል እሴቱን ጠብቆ ለትውልድ እንዲሸጋገር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል – እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

By Mikias Ayele

January 11, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀላባ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል “ሴራ” ለቀጣይ ትውልድ እንዲሸጋገር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል አሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፡፡

የሀላባ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል “ሴራ” በዛሬው ዕለት በሃላባ ቁሊቶ ከተማ ተከብሯል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ እንደ ሀገር የተጀመረው የጋራ ትርክትን የመገንባት ሂደትና የሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ የጋራ ጥረት ማድረግ ይገባል፡፡

ማንነትና ኢትዮጵያዊ አንድነት ሚዛናቸውን ጠብቀው የሚሄዱ ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ÷ በመደመር  እሳቤ ሁሉም ለሀገር ልማት እንዲተጋ ጥሪ አቅርበዋል።

የሀላባ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል “ሴራ”ለቀጣይ ትውልድ እንዲሸጋገር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልመሀዲ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ ሀብቶችን የተጎናፀፈች ሀገር መሆኗን አውስተዋል፡፡

“ሴራ” በአብሮነትና በመደጋገፍ የሚከበር በዓል መሆኑን ጠቅሰው፥ እሴቱን ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ለማሸጋገር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ቋንቋዎች፣ የግጭት አፈታት እሴቶችንና ሌሎች ባህሎችን እንዲጠበቁ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

ሴራ በሃላባ ብሔረሰብ ለዘመናት ተጠብቆ የቆየና ለማህበረሰቡ ያልተፃፈ ህገ መንግስት በመሆን ሲያገለግል እንደነበር የገለጹት ደግሞ የሀላባ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሁዲን ሁሴን ናቸው፡፡

በዓሉ ማህበራዊ ትስስር የሚጠብቅበትና መደጋገፍና መረዳዳት መገለጫው የሆነውን የሚሻላ ስርዓትን ጨምሮ በርካታ እሴቶችን ያቀፈ መሆኑን አስረድተዋል።

በብርሃኑ በጋሻው