የሀገር ውስጥ ዜና

በክልሉ የህግ የበላይነትን በማስከበር ልማትን ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ ነው – ወ/ሮ ዓለሚቱ ኡሞድ

By Adimasu Aragawu

January 12, 2026

‎አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጋምቤላ ክልል የህግ የበላይነትን በማስከበር የልማት ስራዎችን ይበልጥ ለማጠናከር የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ።

የጋምቤላ ክልል የመንግሥት ሰራተኞች በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋምቤላ ከተማ የውይይት መድረክ አካሂደዋል።

ወ/ሮ ዓለሚቱ ኡሞድ በዚህ ወቅት÷ በክልሉ የህግ የበላይነትን በማስከበር የልማት ስራዎችን ይበልጥ ለማጠናከር የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በዚህ ሂደት የመንግሥት ሰራተኞች ተሳትፎና ትብብር ወሳኝ መሆኑን አንስተው÷ በሁሉም ረገድ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ማስቀጠልና የአገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ፈጣንና ቀልጣፋ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

የሚነጣጥሉ እሳቤዎችን በመተው አሰባሳቢና የወል ትርክቶችን በመገንባት ረገድ የመንግሥት ሰራተኞች ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ የሚጥሩ አካላትን በመከታተል በህግ ተጠያቂ የማድረግ፣ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥና የልማት ስራዎችን ለስኬት የማብቃት ጉዳይ በቀጣይ በልዩ ትኩረት ይሰራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።