የሀገር ውስጥ ዜና

ለአህጉራዊ ግቦች መሳካት ቁልፍ ሚና የሚጫወተው የውሃ ሀብት …

By Yonas Getnet

January 12, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ የውሃ ሀብት ለአፍሪካ አህጉር ግቦች መሳካት ቁልፍ ሚና ይጫወታል አሉ።

‘ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት’ በሚል መሪ ሀሳብ 51ኛው የአፍሪካ ሕብረት የቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ ከዛሬ ጀምሮ በሕብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በስብሰባው የአፍሪካ ሕብረትና የሕብረቱ ተቋማት አመራሮች፣ የሕብረቱ አባል ሀገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ተሳትፈዋል።

ስብስባው ከየካቲት 4 እስከ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለሚካሄደው 48ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ እና ለ39ኛው የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ ረቂቅ አጀንዳዎች ላይ ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል።

የኮሚሽኑ ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በመድረኩ እንዳሉት፤ የዘንድሮ የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ትኩረት የውሃ ሀብት ላይ ነው።

የህልውና ጉዳይ ላይ ወሳኝ የሆነው የውሃ ሀብት አህጉራዊ ግቦችን ለማሳካት ቁልፍ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

በብራዚል የተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤ (ኮፕ30) ለውሃ ሀብት ትኩረት በመስጠት አጀንዳ አደርጎ እንደመከረበት አስታውሰው፤ የውሃ ሀብት አቅርቦት እና ደህንነት አህጉራዊ አጀንዳ እንደሆነም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በምታስተናግደው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤ (ኮፕ32) የውሃ ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ኮፕ32ን ለማዘጋጀት በመመረጧ በድጋሚ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ሊቀመንበሩ፤ ህብረቱ ለጉባኤው ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።