ጤና

ውጤታማነትና ተጠያቂነትን መሰረት ያደረጉ የጤና ልማት ስራዎች…

By Adimasu Aragawu

January 12, 2026

‎አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውጤታማነትና ተጠያቂነትን መሰረት ያደረጉ የጤና ልማት ስራዎች ተግባራዊ እየተደረጉ ናቸው አለ የክልሉ ጤና ቢሮ። ‎ ቢሮው በክልሉ የጤና አገልግሎትን በመሰረታዊነት ማሻገር የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና “ጠንካራ የአመራር ግንባታ ለውጤታማ የጤና ስርዓት” በሚል መሪ ሐሳብ ለዘርፉ አመራሮች እየሰጠ ይገኛል። ‎‎ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ውጤታማነትንና ተጠያቂነትን መሰረት ያደረጉ የጤና ልማት ስራዎች በክልሉ ተግባራዊ እየተደረጉ ናቸው። ‎‎ ‎የአቅም ግንባታ ስልጠናው የተጠናከረ የጤና ሥርዓት መፍጠር ላይ ያተኮረ መሆኑን አንስተው÷ ባለቤትነትን መፍጠርና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል። ‎ ‎በክልሉ የጤናውን ዘርፍ ለማሻገር ተግዳሮት የሆኑ 15 ጉዳዮች በሳይንሳዊ ጥናት መለየታቸውን ጠቅሰው÷ ለዚህም 12 ስትራቴጂካዊ መፍትሄዎች በጥናቱ መቅረባቸውን ጠቁመዋል። ‎ ‎ስልጠናውም ከተደረገው ሳይንሳዊ ጥናት መነሻ መዘጋጀቱን አመላክተዋል።

‎በክልሉ የሕብረተሰቡን ተሳትፎ በማሳደግ በርካታ የጤና ልማት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙና የጤና ተቋማትን ዲጂታላይዝ በማድረግ አገልግሎቶቹ ከወረቀት ነጻ ለማድረግ የሚያስችሉ አበረታች ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ‎ ‎ከዛሬ ጀምሮ ለስምንት ቀናት በሚሰጠው ስልጠና ከክልሉ ሁሉም መዋቅሮች የተወጣጡ የዘርፉ አመራሮች መሳተፋቸውን የቢሮ ኮሙኒኬሽን ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ አመላክቷል።