አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በሁሉም አካባቢዎች ዓመቱን ሙሉ ማምረት ይቻላል አሉ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር)።
ዋና ዳይሬክተሩ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ የኢኮኖሚው እና የህዝቡ ዕድገት ፍላጎቱን ስለሚጨምረው ኢትዮጵያ ምርታማነቷን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ አለባት።
የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ዕድሎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ከዚህ ውስጥ በተለያዩ የውሃ አማራጮች ዓመቱን ሙሉ የማምረት አቅምን መጠቀም አንደኛው ዕድል መሆኑን ተናግረዋል።
በግብርና ዘርፍ የተገኘው ውጤት ለቀጣይ ትልቅ ተስፋ በመሆኑ የገጸ ምድር እና የከርሰ ምድር የውሃ ሃብትን በመጠቀም እየተከናወነ ያለውን የመስኖ ልማት በሁሉም የገጠር ቀበሌዎች ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ ሁሉም አካባቢዎች የመስኖ አቅም አለ ያሉት ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር)፤ ወንዝ እና የጉድጓድ ውሃ በሌለባቸው አካባቢዎች የዝናብ ውሃን በመያዝ በበጋ ወቅት መጠቀም ይቻላል ብለዋል።
ቻይና የዝናብ ውሃን በመያዝ በዋሻ መልክ በተዘጋጁ ግዙፍ የውሃ ማጠራቀሚያዎች አስቀምጣ ዝናብ በሌለበት ወቅት ለእርሻ እንደምትጠቀም በአብነት አንስተው፤ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ አቅም መጠቀም የምትችልበት ዕድል እንዳለ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በአንድ የክረምት ወቅት 110 ኪሎ ሜትር ኩዩብ የዝናብ ውሃ ታገኛለች በማለት ገልጸው፤ ይህ ከፍተኛ የውሃ መጠን ሳይባክን ጥቅም ላይ እንዲውል መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በዚህም በቴክኖሎጂ ላይ ኢንቨስት በማድረግ እና አርሶ አደሩ ስልጠና እንዲያገኝ በማስቻል በሁሉም አካባቢዎች ክረምት ከበጋ በማምረት ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ እንደሚቻል አስገንዝበዋል።
በአቢይ ጌታሁን