የሀገር ውስጥ ዜና

ምርጫውን በሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል – አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

By Adimasu Aragawu

January 13, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማከናወን የሚያስችል ዝግጅት አድርጓል አሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ።

ምክር ቤቱ ሀገር አቀፍ የሕግ አውጪዎች የጋራ ምክክር መድረክ የመንግሥታት ግንኙነት ስርዓትን ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1231/2013 መሰረት በቢሾፍቱ ከተማ እያካሄደ ነው።

አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ሀገር አቀፍ የሕግ አውጪዎች የጋራ ምክክር መድረክ ዘላቂ ሰላምና ልማትን በማረጋገጥ የአንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማሕበረሰብ ለመገንባት ወሳኝ ነው።

በዚህም በዘንድሮው የምክክር መድረክ ወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ተነስተው ከፌደራልና ክልል ህግ አውጪዎች ጋር ውይይት ይደረግባቸዋል ብለዋል።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅትና የምክር ቤቶች ሚና፣ የፐብሊክ በጀትና የፋይናንስ ትንተናና ጥናት ሰነድ እና የሕግ ኦዲት ሰነድ ላይ ምክክር እንደሚደረግም ገልጸዋል።

መንግሥት ለጠቅላላ ምርጫ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የግብዓት አቅርቦትና ሚና በተመለከተ ምክክር ማድረጉን ተናግረዋል።

መንግሥት ምርጫውን ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማከናወን አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የክልል ምክር ቤቶች የዘንድሮው ምርጫ ከ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ በተሻለ ለመፈፀም የማስተባበር ሚናቸውን በብቃት መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

ምርጫውን ስኬታማ ለማድረግ አቅማችንን መገንባት ይገባናል ያሉት አፈ ጉባኤው÷ ሀገር አቀፍ የሕግ አውጪዎች የጋራ ምክክር መድረክ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በርካታ ሪፎርሞች ማድረጉን በማንሳት÷ የክትትልና ቁጥጥር፣ የሕዝብ ውክልና ሥራ በብቃት መወጣት የሚያስችል ሥራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገር አቀፍ የሕግ አውጪዎች የጋራ የምክክር መድረክ የጋራ ትርክትን መገንባትና ግልፅነትን መፍጠር የሚያስችል ምህዳር ማስፈን እንደሚያስችል መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።