ቢዝነስ

የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለውጭ ባለሃብቶች አመቺ የኢንቨስትመንት ስነምህዳር ፈጥሯል – ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)

By Hailemaryam Tegegn

January 13, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገችው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለውጭ ባለሀብቶች አመቺ የኢንቨስትመንት ስነምህዳር ፈጥሯል አሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፡፡

ከ35 በላይ የጃፓን ኩባንያዎች የተውጣጡ ልዑካን የተሳተፉበት የኢትዮ-ጃፓን የቢዝነስ ፎረም በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ፎረሙ የሁለቱን ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ጉልህ ሚና እንደሚኖረው የተገለጸ ሲሆን፥ ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።

ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ በአምራች ዘርፉ፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ በግብርና፣ በማዕድን፣ በአገልግሎትና በሌሎች ዘርፎች አመቺ የኢንቨስትመንት እድሎችን ፈጥሯል።

መንግስት በተገበረው ጥቅል የሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ለውጭ ባለሀብቶች አመቺ ስነምህዳር ከመፍጠሩ ባሻገር ኢትዮጵያ ቀዳሚ የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች መምጣቷን አንስተዋል።

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ጨምሮ ሌሎች ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የንግድ ስምምነቶችን መተግበሯ የንግድና ኢንቨስትመንት ፍሰቱ እንዲሳለጥ በማድረግ ለውጭ ባለሀብቶች ትልቅ የገበያ ትስስር እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በምታደርገው ጥረት ከጃፓን ጋር የሁለትዮሽ የንግድ ስምምነትን በቴክኒክ ደረጃ ማጠናቀቋን አስታውሰው፥ ስምምነቱ በፍጥነት በፊርማ መቋጨት እንዳለበት ገልጸዋል።

በተለዩዩ ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ለሚሰማሩ የጃፓን ባለሀብቶች መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ኩኒሚትሱ አያኖ በበኩላቸው፥ ሀገራቸው የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስሩን ለማጠናከር ከ50 በላይ አባላት ያሉት ልዑክ መላኳን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ በተፈጠረው ምቹ የኢንቨስትመንት ስነምህዳር በርካታ የጃፓን ባለሀብቶች በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት አላቸው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋነኛ መውጫና መግቢያ በር መሆኗን በማስታወስ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ትግበራውን፣ የፖሊሲ ማሻሻያዎችንና በቂ የኃይል አቅርቦት መኖሩን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ለሚፈልጉ ባለሀብቶች መንግስታቸው ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ገልጸው፥ የሁለቱ ሀገራት የንግድ ማህበረሰብ አባላት የጥምር ኢንቨስትመንት ትስስር በመፍጠር የሀገራቱን ግንኙነት እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

በመሳፍንት ብርሌ