አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ባቱ ከተማ የሚገኘው ደምበል ሃይቅ ለቱሪስት መስሕብነት ተመራጭ ከሆኑ ስፍራዎች በቀዳሚነት ይጠቀሳል።
ሃይቁ የጥምቀት በዓል በመጣ ቁጥር ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ የሚደምቅ ሲሆን÷ በውስጡ ገሊላ፣ ደብረሲና፣ ደብረፂዮን፣ ጠደቻና ፉንድሮ የተሰኙ ደሴቶችን ይዟል።
በደሴቶቹም የአቡነ ተክለሃይማኖት፣ ቅዱስ ሚካኤል፣ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም፣ አርባዕቱ እንስሳትና ፀዴቻ አቡነ አብርሃም ገዳማት ይገኛሉ።
እነዚህ ገዳማት እና አብያተ ክርስቲያናት የጥምቀት በዓልን በደምበል ሃይቅ ላይ የሚያከብሩ ሲሆን÷ በቦታው ለየት ባለ መንገድ የሚከበረው የጥምቀት በዓልም ለቱሪዝም ዕድገትና ቱሪስቶችን ከመሳብ አንጻር ከፍተኛ አዎንታዊ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል።
በመሆኑም ከተማዋ የዘንድሮ የጥምቀት በዓል በድምቀት እንዲከበር ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጓን የባቱ ከተማ ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ተሚማ በሪሶ ገልጸዋል።
ባቱ ከተማ የቱሪዝም ከተማ ናት፤ ትልቁ የቱሪዝም ሃብቷ ደግሞ የደምበል ሃይቅ ነው ያሉት ኃላፊዋ÷ ሃይቁም 56 ሺህ ሄክታር ቦታ እንደሚሸፍንና ትልቅ የአዕዋፋት ደሴት እንደሚገኝበት አስረድተዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በሃይቁ ዙሪያ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት በቱሪዝም ዘርፍ የተሻለ ገቢ ለማግኘት እየሰራ መሆኑን ገልጸው÷ ወጣቶችም ተደራጅተው ዓሣ በማምረት ህይወታቸውን እየቀየሩ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
የጥምቀት በዓል በደምበል ሐይቅ ላይ ሲከበር መቆየቱንና በዓሉን ለመታደምም በርካታ ቱሪስቶችና እንግዶች ወደ ከተማዋ እንደሚመጡ ጠቁመዋል።
በዓሉን ለማክበር ወደ ከተማዋ የሚመጡ ቱሪስቶች እና እንግዶችን ለመቀበል ሆቴሎች፣ ደሴቶችን ሄደው መጎብኘት እንዲችሉ የጀልባ አቅርቦት እንዲሁም ከተማዋን ጽዱ በማድረግ ዘርፈ ብዙ ዝግጅቶች መደረጋቸውን አንስተዋል።
በሶስና አለማየሁ