አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢትዮጵያ ዘመናዊ የችርቻሮ ንግድን ለማስፋፋትና የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ ዕድል ፈጥሯል አሉ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ።
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር የሚገኘው ኩዊንስ ሱፐርማርኬት የንግድ ስያሜን ከነሙሉ አሰራሩ የመጋራት (የፍራንቻይዝ) እና የአቅርቦት አጋርነት ስምምነት ከዓለም አቀፍ የችርቻሮ ንግድ ተቋም ካርፎር (Carrefour) ጋር ተፈራርመዋል።
አቶ አህመድ ሺዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ ያደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ተጨባጭ ውጤቶችን እያስገኘ ነው።
በማሻሻያው የችርቻሮ ንግድ ለውጭ ገበያ ክፍት መደረጉን አስታውሰው÷ ይህን ተከትሎ አቅም ያላቸው ተቋማት እየመጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ ዘመናዊ የችርቻሮ ንግድን ማሳለጥ የሚያስችሉ አሰራሮች መዘርጋታቸውን ገልጸው÷ የፈረንሳዩ ካርፎር ግሩፕም የዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ተቋማቱ ያደረጉት ስምምነት ኢትዮጵያውያን ጥራት ያላቸው ምርቶችን እንዲያገኙና የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም ገበያ እንዲተዋወቁ ዕድል ይፈጥራልም ነው ያሉት።
በስምምነቱ መሠረት 13 የኩዊንስ ሱፐርማርኬት ቅርንጫፎች ወደ ካርፎር ብራንድ የሚቀየሩ ሲሆን÷ የመጀመሪያዎቹ መደብሮች በፈረንጆቹ 2026 አጋማሽ ሥራ ይጀምራሉ ተብሏል።
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጀማል አህመድ በበኩላቸው÷ ስምምነቱ የሀገር ውስጥ ምርትን ከዓለም አቀፍ የንግድ እና የጥራት ደረጃዎች ጋር ለማጣጣም እንደሚረዳ አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ዕድል የሚከፍት መሆኑን ጠቁመው÷ በስምምነቱ መሰረት ነባር የኩዊንስ ሱፐር ማርኬቶችን በካርፎር ስያሜ ከመቀየር ባሻገር በተለያዩ የሀገሪቷ ከተሞች ቅርንጫፎችን የማስፋፋት ዕቅድ መያዙን አመልክተዋል፡፡
ሚድሮክ የሚያመርታቸውን እንደ ቡና፣ ሻይ፣ ቅመማ ቅመም፣ አበባና ፍራፍሬ ያሉ ምርቶች በካርፎር ዓለም አቀፍ መረብ አማካኝነት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።
የካርፎር ኢንተርናሽናል ፓርትነርሺፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፓትሪክ ላስፋርጉስ ነባር የኩዊንስ ሱፐርማርኬቶችን በፍጥነት በካርፎር ስያሜ ስር ከመቀየር በዘለለ እስከ ፈረንጆቹ 2028 ተጨማሪ 17 የችርቻሮ መደብሮችን ለመክፈት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡
በዘርፉ ሚድሮክ ያለውን የላቀ እውቀትና የካርፎርን ዓለም አቀፍ ልምድ በማቀናጀት ለኢትዮጵያውያን ደንበኞች ጥራት ያላቸው ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ እንሰራለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን ገልጸው÷ በተለይም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በርካታ ዘርፎች ለውጭ ባለሃብቶች እንዲከፈቱ ዕድል መፍጠሩን አንስተዋል።
ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በቀላሉ ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ኢትዮጵያ ታዋቂ የሆነችባቸውን ቡናን የመሳሰሉ ምርቶች ለዓለም ገበያ በብዛትና በከፍተኛ ጥራት እናቀርባለን ብለዋል።
ካርፎር ግሩፕ በ40 ሀገራት መደብሮች እንዳሉት ጠቅሰው÷ በኢትዮጵያ ሥራ መጀመሩ በዓለም አቀፍ ገበያ የሀገሪቷን ምርቶች ያስተዋውቃል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ካርፎር በዓለም ዙሪያ ከ15 ሺህ በላይ መደብሮች ያሉትና በፈረንጆቹ 2024 ብቻ 94 ነጥብ 6 ቢሊየን ዩሮ ገቢ ያስመዘገበ ግዙፍ ኩባንያ ነው።