ስፓርት

የአፍሪካ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ

By Yonas Getnet

January 14, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ይካሄዳሉ።

ዛሬ ምሽት 2፡00 ሰዓት ላይ በሚደረገው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ተፋላሚዎቹ ሴኔጋል እና ግብጽ ይገናኛሉ።

በዚህ ጨዋታ ላይ የቀድሞ የቡድን አጋር የነበሩት የሴኔጋሉ ሳዲዮ ማኔ እና የግብጹ ሞሐመድ ሳላህ ሀገራቸውን ለፍጻሜው ለማብቃት ከባድ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ባደረጓቸው ያለፉት 15 ጨዋታዎች ግብፅ 7 ጨዋታዎችን ስታሸንፍ ሴኔጋል 5ቱን ማሸነፍ ችላለች፤ በ3ቱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታው ምሽት 5፡00 ሰዓት ላይ ቀጥሎ ሲካሄድ የውድድሩ አዘጋጅ ሞሮኮ እና ናይጄሪያ ይገናኛሉ።

ከ22 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰችው ሞሮኮ በሀገሯ እና ደጋፊዎቿ ፊት ወደ ፍጻሜው ለማለፍ ብርቱ ፉክክር ታደርጋለች።

በውድድሩ ጠንካራ ከነበሩት ቡድኖች መካከል አንዷ የሆነችው ናይጄሪያ በደጋፊዎቿ ፊት የምትጫወተውን ሞሮኮ ለመርታት ዝግጁ ሆና ወደ ሜዳ ትገባለች።