አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ለፌደራል ስርዓቱ መረጋገጥ ከፍ ያለ ሚና እየተጫወተ ነው አሉ።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተከበረው 20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በስኬት እንዲጠናቀቅ የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት የዕውቅና መርሐ ግብርና የአፈጻጸም ግምገማ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በዓሉ በብሔር ብሔረሰቦች መካከል የእርስ በእርስ ትውውቅ እንዲጎለብት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
በተለይም በለውጡ ዓመታት እውነተኛ የፌደራሊዝም ስርዓትን መሰረት አድርጎ እንዲከበር በመደረጉ ለፌደራል ስርዓቱ መረጋገጥ ከፍ ያለ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የታላቁ ሕዳሴ ግድብን በማጠናቀቅና የጉባ ብስራቶችን በማብሰር በሁሉም መስክ የማንሰራራት ጉዞን በጀመረችበት እንዲሁም ምክክር በሚደረግበት ወቅት በመከበሩ ልዩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በዓሉ የተከበረበት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀገራዊ ለውጡ ራስን በራስ የማስተዳደር ዕድል ያገኘ ክልል መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህም የፌደራል ስርዓቱ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ባለፈው ህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ መከበሩ ይታወሳል።
በሰለሞን በየነ