አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የለውጡ መንግስት ቱሪዝምን እንደ አንድ የኢኮኖሚ መሰረት በመውሰድ በትጋት ሰርቷል አሉ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ ከለውጡ ጋር በመጣ የቱሪዝም ንጋት እየደመቀችና እየለማች ነው፡፡
የኢትየጵያ የዘመናት የቱሪዝም መዝገብ ሲገለጥ የሚነበበው በልኩ ያልደመቀ መልክዓ ተፈጥሮ፣ በወጉ ያልተገለጠ የታሪክ ግርማ፣ ሌማት ሆኖ ያልቀረበ ሃብትና ውበት መሆኑን አንስተዋል፡፡
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በቱሪዝም ዘርፍ የመጣው ለውጥ ይህንን የዘመናት ችግር ከመሰረቱ በመናድ አዲስ የቱሪዝም ልማት አምዶችን ያቆመ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የለውጡ መንግስት ቱሪዝምን እንደ አንድ የኢኮኖሚ መሰረት በመውሰድ በትጋት መስራቱን አስታውሰው፥ አሁን የድካሙ ፍሬ እየተሰበሰበና የሀገራዊ ጥረቱ አዝመራ እየታጨደ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዘርፉን በጠራ ራዕይ ተመልክተው ለቱሪዝም የነበረውን እሳቤ ከማስተካከል ጀምሮ ሀገር እና ትውልድን ማዕከል ያደረገ አመራር በመስጠት የሰሩት ስራ የስኬቱ በር ከፋች ነው ብለዋል፡፡
ዛሬ በቱሪዝም ዘርፍ እያየን ያለነው ስኬት እንደ ቀን ንጋት የሚቆጠር የስኬት አሃዱ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡