የሀገር ውስጥ ዜና

በምስራቅ ሸዋ ዞን ከ370 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት እየተሰራ ነው

By Hailemaryam Tegegn

January 15, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን በዚህ ዓመት ከ370 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት እየተሰራ ነው አለ የዞኑ ግብርና ጽ/ቤት።

የጽ/ቤቱ ምክትል ኃላፊ አብነት ዘገየ እንዳሉት፥ በዞኑ ሰብሎችን ጨምሮ አትክልትና ፍራፍሬ እየተመረቱ ሲሆን በአመት ሶስት ጊዜ ማምረት ተችሏል።

በዞኑ አርሶ አደሩን ከማብቃትና ግብርናውን ከባህላዊ አስተራረስ ከማሻገር አንጻር ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ ስንዴን በኩታ ገጠም ማምረት ዘንድሮ ለ6ኛ ጊዜ መሆኑን ጠቅሰው፥ በተለይም በስንዴ ምርት ዙሪያ የአርሶ አደሩን ግንዛቤ ለማሳደግ ተቋሙ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አንስተዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ሀስ የሚባል የተሻለ ምርት የሚያስገኝ አቮካዶ ዝርያ ለአርሶ አደሮች ማቅረቡን የገለጹት ኃላፊው፥ አርሶ አደሮች በተፈጠረላቸው ግንዛቤ ተጠቅመው የሚያኙትን ምርት ከምግብ ፍጆታነት ባለፈ የገቢ ምንጭ በማድረግ ሀብት ማፍራት ችለዋል ነው ያሉት፡፡

በተከታታይነት በተሰሩ ስራዎች በስራ የሚያምንና ራሱን የሚለውጥ አርሶ አደር እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸው፥ አደይ በተሰኘ አገልግሎት አማካኝነት ወጣቶች አቅማቸውን አሳድገው የሚለወጡበት መንገድ መፈጠሩንም አብራርተዋል።

በተያዘው ዓመት በዞኑ ከ370 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት እየተሰራ ሲሆን፥ ለዚህም ከ700 በላይ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪዎች ዝግጁ መሆናቸውን አንስተዋል።

እሴትን ጨምሮ ከመጠቀም አንጻር 80 በመቶ የሚሆኑት አርሶ አደሮች በከታ ገጠም እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በሶስና አለማየሁ