አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የታሪካዊ ኪነ ሕንጻዎች እድሳትና የከተሞች የኮሪደር ልማት የኢትዮጵያን ውበት ይበልጥ እየገለጠ ነው አሉ የሀገር ሽማግሌዎች።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎችና የኪን ኢትዮጵያ አባላት የፋሲል ዓብያተ መንግሥታትን ጎብኝተዋል።
ሸዊት ሻንካ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ መንግሥት ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሃብቶችን መጠበቅና ማልማት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።
የታሪካዊው ፋሲል ዓብያተ መንግሥታት እድሳትም የኪነ ሕንጻውን ውበት ይበልጥ የገለጠ መሆኑን አውስተዋል።
በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉ የሀገር ሽማግሌዎች በበኩላቸው፥ የፋሲል ዓብያተ መንግሥታት ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ የታደሰበት ሁኔታ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፋሲል ዓብያተ መንግሥታት በተደረገለት እድሳት ልዩ ገጽታ እንዲጎናጸፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመሥግነዋል።
እየተከናወኑ የሚገኙት የታሪካዊ ኪነ ሕንጻዎች እድሳትና የከተሞች የኮሪደር ልማት የኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻነት እንደሚያሳድጉ ተናግረዋል።
ሥራዎቹ በየአካባቢው ያለውን ድብቅ ውበት ከማጉላት ባለፈ ከተሞች ምቹና ዘመናዊ እንዲሆኑ ያስችላሉ ነው ያሉት።
የሕዝቦችን ትስስርና አብሮነት ይበልጥ ለማጠናከር የወል ትርክትን መገንባት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዚህ ረገድ ኪን ኢትዮጵያ በውጭና በሀገር ውስጥ የኢትዮጵያን ቱባ ባህል፣ እሴትና ወግ በማሳየት እያበረከተው ያለው አስተዋጽኦ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት በእናትዋ ጎንደር እየተካሄደ የሚገኘው የኪን ኢትዮጵያ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር መድረክ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
የሃሳብ ልዩነትን በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት መፍታት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ለዚህም የሀገር ሽማግሌዎች የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በመላኩ ገድፍ