የሀገር ውስጥ ዜና

ኪን ኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊነትን ለመገንባትና ገዢ ትርክትን ለማስረጽ ጉልህ ሚና አለው – ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ

By Mikias Ayele

January 15, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ‎የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ‘ኪን ኢትዮጵያ’ ሕብረ ብሔራዊነትን ለመገንባትና ገዢ ትርክትን ለማስረጽ ጉልህ ሚና አለው አሉ።

‘ኪን ኢትዮጵያ’ የጥምቀት በዓልን ለማክበር በተሞሸረችው ጎንደር ከተማ መስቀል አደባባይ የባህልና የኪነ ጥበብ ሥራዎችን እያቀረበ ነው።

በመርሐ ግብሩ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ መልካሙ ጸጋዬ፣ የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው እና ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ታድመዋል።

ሸዊት ሻንካ በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥ ኪን ኢትዮጵያ የኢትዮጵያን ብዝሃ መልክ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት በማሳየት አበረታች ሥራዎችን እያከናወነ ነው።

በታሪካዊቷ ጎንደር የተሰናዳው የኪን ኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ዝግጅት የሕዝቦችን ትስስርና አብሮነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑን አውስተዋል።

ኪነ ጥበብ ሕብረ ብሔራዊነትን ለመገንባትና ገዢ ትርክትን ለማስረጽ ጉልህ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ድንቅ ባህሎች፣ ትውፊቶችና ቅርሶች መኖራቸውን አውስተዋል።

ኪነ ጥበባት የሀገር መገለጫ ናቸው ያሉት ሚኒስትሯ፥ ያላቸውን ጠቀሜታ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በበኩላቸው ፥  የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ወደሆነችው ጎንደር ከተማ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል።

ጎንደር የኪነ ጥበብ መናገሻ ከተማ በመሆኗ ለኪን ኢትዮጵያ ሥራዎችና ለሌሎች ኪነ ጥበብ ክዋኔዎች ምቹ መሆኗን አውስተዋል።

ለዚህም በጎንደር  የኪነ ጥበብ መንደር ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

በአማራ ክልል ብዝሃ ባህል፣ ቋንቋ እና ሃይማኖት ተቻችሎ እና ተከባብሮ እንደሚኖሩ የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ መልካሙ ጸጋዬ ናቸው።

የተፈጠሩ ስሑት ትርክቶችን በማክሰም ገዢ ትርክትን ለማስረጽ በቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኝ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኪነ ጥበብ  የሀገር ገጽታን ከመገንባት ባለፈ ሀገራዊ ፈተናዎችን በድል ለመወጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታልም ነው ያሉት።

በዚህ ረገድ ኪን ኢትዮጵያ የሕዝቦችን አብሮነት ለማጠናከር የጀመረው ሥራ የሚበረታታ መሆኑን አመልክተዋል።

በመላኩ ገድፍ