ቴክ

የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፉ ማሻሻያ ለፋይናንስ ተደራሽነትና ቅልጥፍና ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው – የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን

By Mikias Ayele

January 15, 2026

የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፉ ማሻሻያ ለፋይናንስ ተደራሽነትና ቅልጥፍና ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው አሉ ‎የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ (ኢ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ቁልፍ የመንግሥት ፋይናንስና ሌሎች የፋይናንስ ዘርፍ ተቋማትን ያሰባሰበው የኢትዮጵያ የፋይናንስ እመርታ ኮንፈረንስ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡

ባልቻ ሬባ (ኢ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የሚያስችል ተቋማዊ አሰራርን መከተል ወሳኝ ነው። ‎

ለዚህም በዘርፉ የሚሰማሩ አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ መስጠት፣ መከታተልና መቆጣጠር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፥ ዘርፉ በራሱ እድገት እንዲያስመዘግብ ከማድረግ ባለፈ ለሌሎች ዘርፎች እድገት አስቻይ በመሆኑ ተቋማቸው በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።‎

‎አሁን ላይ በዘርፉ የተደረጉ ማሻሻያዎች አዳዲስ ኦፕሬተሮችን ወደ ስራ ከማስገባት ጀምሮ የኔትዎርክ ተደራሽነትና የሞባይል ተጠቃሚዎችን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ተችሏል ነው ያሉት።

በተለይም የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፉ ለፋይናንስ ተደራሽነት፣ ቅልጥፍናና ዘመናዊ አገልግሎት እየሰጠው ያለው አገልግሎት ተጠቃሽ መሆኑን አንስተዋል፡፡