የሀገር ውስጥ ዜና

ማንኛውንም ዓይነት ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች የመቋቋም አቅማችንን በማሳደግ ለዘላቂ ልማት እንተጋለን – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By Adimasu Aragawu

January 16, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ማንኛውንም ዓይነት ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን በመከላከልና የመቋቋም አቅማችንን በማሳደግ፣ በራሳችን ጥረትና ድካም እየተረዳዳን ለዘላቂ ልማት እንተጋለን አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

ልመናና ተረጂነት ስንፍናን የሚያስፋፉ፣ ሰብአዊ ክብርን የሚነኩና ዘላቂ ልማትን የማያረጋግጡ ተግባራት ናቸው ያሉት ከንቲባዋ÷ በመሆኑም የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት የግድ ይላል ብለዋል።

በተለይም የትምህርትና የሃይማኖት ተቋማት ይህንን የተረጂነትና የልመና አስተሳሰብ በመለወጥ ረገድ ዋነኛ ተዋናይ መሆን ይጠበቅባቸዋልም ነው ያሉት።

ይህንን ተግባር ለማሳለጥ የአዲስ አበባ የአደጋ ስጋት ምክር ቤት የአደጋ ተጋላጭነትን በማስቀረት፣ የአደጋ ዝግጁነትን በማጠናከርና ምላሽ ሰጪነትን በማሳደግ በኩል እንደ ሀገር የተጀመረውን የአሰራር ለውጥ ለማስቀጠል ዛሬ ስራውን በይፋ ጀምሯል ብለዋል።

ምክር ቤቱ የተረጂነትን አሉታዊ አስተሳሰብ ለመለወጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥም ግንባር ቀደም ሚናውን ለመወጣት የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል።