አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአልጄሪያ ሳተላይት ማምጠቅ የአፍሪካን ህዋ ሳይንስ ከፍተኛ እድገትና የጂኦስፓሻል አቅሞችን ያሳያል አሉ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ።
አልጄሪያ “አልሳት-3 ኤ” የተሰኘች የመሬት ምልከታ ሳተላይትን በተሳካ ሁኔታ ወደ ህዋ ማምጠቋን ተከትሎ ሊቀ መንበሩ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም የሳተላይት ማምጠቅ የአልጄሪያን በህዋ ሳይንስ አመራር እና የሳተላይት ቴክኖሎጂዎችን ለዘላቂ ልማት፣ ለአካባቢ ጥበቃ ክትትል፣ ለአደጋ ስጋት ቅነሳ እንዲሁም በመረጃ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ለማውጣት ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ አመልክተዋል።
ሊቀመንበሩ የአልጄሪያ የተሳካ የመሬት ምልከታ ሳተላይት ማምጠቅ የአፍሪካ ህዋ ሳይንስ ከፍተኛ እድገት እና የጂኦስፓሻል አቅሞችን ያሳያልም ነው ያሉት።
ከሳተላይቱ የመሬት ምልከታ የተገኘው መረጃ ከአጀንዳ 2063፣ ከአፍሪካ የጠፈር ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ጋር በተጣጣመ መልኩ ለሀገራዊና አሕጉራዊ ጉዳዮች የበኩሉን አስተዋፅኦ ያበርክታል ሲሉም ገልጸዋል።
አልጄሪያ የምታከናውናቸው ቀጣይ ኢንቨስትመንቶችና የህዋ ጉዞዎች የአፍሪካን የጋራ እድገት የሚያግዙ እንደሆነም አንስተዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ሳተላይት ማምጠቅን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ ትብብሮችን ለመቀበል ዝግጁ መሆኑንም አጽንዖት ሰጥተዋል።
በሶስና አለማየሁ