የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ የተገኙ 11 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

By Mikias Ayele

January 17, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ በኮንስትራክሽን ግብአት አከፋፋይ ነጋዴዎች ላይ በተካሄደ የታክስ ኦፕሬሽን ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ የተገኙ 11 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች ቢሮ ለፋና ዲጂታል እንዳስታወቀው÷ በትናንትናው ዕለት መርካቶን ጨምሮ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች የኮንስትራክሽን ግብአቶች በሚሸጡ የንግድ ድርጅቶች ላይ የተጠና የታክስ ኦፕሬሽን ተካሂዷል፡፡

ከድርጊቱ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያላቸው 11 የንግድ ስራው ባለቤቶችና ሽያጩን ያለደረሰኝ ሲያከናውኑ የነበሩ ሰራተኞች የመንግስትን ግብር ለመሰወር ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ እጅ ከፍንጅ ተይዘው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ነው የተገለፀው፡፡

ቢሮው የኦፕሬሽን ተግባሩን በሌሎችም የንግድ ዘርፎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያሳወቀ ሲሆን፣ የንግዱ ማህበረሰብ ግብይቶችን በደረሰኝ ብቻ እንዲፈፅም አሳስቧል፡፡

በተመሳሳይ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በጎማና በኤሌክትሮኒክስ ነጋዴዎች ላይ በተካሄደ ተመሳሳይ ድንገተኛ ኦፕሬሽን 20 የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ እጅ ከፍንጅ ተይዘው በህግ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል፡፡

ህብረተሰቡም በ7075 ነፃ የስልክ መስመር በመጠቀም መሰል ወንጀሎችን እንዲያጋልጥ ቢሮው ጥሪ አቅርቧል፡፡