አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በትምህርት ቤቶች በዲሲፕሊን የታነጸ ብቁ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር ዘመኑን የዋጀ ሥርዓተ ትምህርት መዘርጋት አስፈላጊ ነው አሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል።
አቶ መላኩ አለበል በጎንደር ከተማ የፋሲለደስ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ አካል የሆነው ባለሁለት ደርብ ዘመናዊ የመማሪያ ህንፃ ግንባታን በዛሬው ዕለት መርቀዋል።
የማስፋፊያ ግንባታው በፋሲለደስ ድምጽ ማህበር አስተባባሪነት በሀገር ውስጥና በውጭ ከሚኖሩ የቀድሞ ተማሪዎች እና ድርጅቶች በተገኘ ድጋፍ ነው የተከናወነው።
አቶ መላኩ አለበል በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ የትምህርት ተደራሽነትን ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት መስራት ይገባል።
የትምህርት ቤቶችን ገጽታ ምቹና ሳቢ በማድረግ የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት ማነሳሳትና የትምህርት ጥራትን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።
ትምህርት አንድን ማሕበረሰብ ለመገንባትና ለማሻገር ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ለዚህም የመምህራንን አቅምና ተጠቃሚነት ማጎልበት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻዎች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው በበኩላቸው፥ በከተማዋ የትምህርት ግብዓት አቅርቦትና መሰረተ ልማት ለማሟላት በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።
የጎንደር ከተማ ታሪካዊነቷን የሚመጥን፣ ውብና ለነዋሪዎች ምቹ እንድትሆን እንዲሁም የቱሪስት መዳረሻነቷን ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ለትምህርት ቤት ግንባታው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋና አቅርበዋል።
ከ100 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ትምህርት ቤቱ 34 የመማሪያ ክፍሎች፣ 5 የአስተዳደርና ሌሎች ክፍሎችን አካትቷል።
በመላኩ ገድፍ