አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገጠር ኮሪደር የአርሶ አደሮችን እና አርብቶ አደሮችን ሕይወት በመለወጥ ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወት ሀገራዊ ሥራ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ዛሬ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ጉራፈርዳ ወረዳ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እና ተጠሪ ተቋማት የተሰሩትን የሞዴል ገጠር ኮሪደር ስፍራ ጎብኝተናል ብለዋል።
ሞዴል ሥራው እያንዳንዳቸው ሳሎን፣ መኝታ ቤቶች፣ የእንስሳት ክፍል እና የውጭ መጸዳጃ ክፍሎች ያላቸው አስር ዘመናዊ ቤቶችን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።
ቤቶቹ ከኤሌክትሪክ መስመር ጋር የተገናኙና የሳተላይት ዲሽ የተገጠመላቸው መሆናቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ጊቢው የዶሮ ማርቢያዎች፣ የእንስሳት በረት፣ የንብ ቀፎዎች ብሎም በፍራፍሬ እና አትክልት የተሞሉ ጓሮዎች አሉት ብለዋል።
የፀሐይ ኃይልን፣ ባዮጋዝ እና ሌሎች የልማት ሥራዎችን በመጠቀም ተቀናጅቶ የተተገበረው የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራ ለማኅበረሰቡ ዘመናዊ፣ ጤናማ፣ ጽዱ እና ለተሻሻለ የአኗኗር ዘይቤ ጠንካራ እድል የሚሰጥ መሆኑንም አመልክተዋል።
ይኽ የለውጥ ሥራ በሁሉም ዘርፍ እንዲስፋፋ ሁሉም የየድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።