አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 16 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 88ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ምክር ቤቱ የተወያየው በመገናኛ ብዙሃን ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ የሚመራበት ራሱን የቻለ የመገናኛ ብዙሃን ፖሊሲ ባለመኖሩ ዘርፉን በብቃት እና በጥራት ማስፋፋትና ሁሉንም ዜጎች የመረጃ ተደራሽ ማድረግ አለመቻሉን በመግለፅ የአገሪቱን የመገናኛ ብዙሃን የሚመራበትና የሚደገፍበት ሀገሪቱም ከምትከተለው የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ፣ ከመሰረታዊ የሰው ልጅ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት እና ህግጋት፣ ከህብረተሰቡ ባህል፣ እሴት፣ አመለካከት እና ፍላጎት እንደዚሁም በዘርፉ ካጋጠመው መሰረታዊ ተግዳሮቶች፣ ከቴክኖሎጂ ውጤቶች እና መሰል ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር የተጣጣመ የፖሊሲ ሰነድ ማዘጋጀት አስፈላጊ በመሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ረቂቅ ፖሊሲ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ማቅረቡ ተመልክቷል።
ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ፖሊሲ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ የተሰጡ ግብዓቶች ተካተው በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል።
በመቀጠለም ምክር ቤቱ የተወያየው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 1186/2012 ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው።
የአዋጁ አንቀፅ 43(1) ተሻሽሎ “አንቀፅ 43(1) በዚህ አዋጅ ምእራፍ 3 ክፍል 1 ፈቃድ ስለማውጣት የተደነገገው ቢኖርም የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸውን እቃዎች በማምረት ወይም አገልግሎት በመስጠት የተሰማራ ማናቸውም ሰው ፈቃድ ባይኖረውም ወይም ባይመዘገብ እስከ የካቲት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸውን እቃዎች ማምረት ወይም ወደ አገር የማስገባት ወይም አገልግሎት የመስጠት ስራ ማከናወን ይችላል።” በሚለው እንዲተካ የማሻሻያ ሀሳብ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲቀርብ ወስኗል።