አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ ለአረጋውያን እናትና አባቶች ጋቢ የማልበስና ማዕድ የማጋራት መርሐ ግብር አከናውነዋል፡፡
ከንቲባዋ በአዲስ አበባ ዘመናዊ የአረጋውያን መጦሪያና መንከባከቢያ ከሰንሻይን ፊላንትሮፒ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ለአረጋውያን እናትና አባቶቻችን ጋቢ የማልበስና ማዕድ ማጋራት አከናውነናል ነው ያሉት።
ከሰንሻይን ፊላንትሮፒ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ባስገነባነው ዘመናዊ የአረጋውያን መጦሪያና መንከባከቢያ ማእከል የሀገር ባለውለታ የሆኑና ድጋፍ የሚሹ አረጋውያን ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ ከተማችን በልማት ሥራዎቿ ሁሉ ታሳቢ አድርጋቸው በቀሪ ዘመናቸው ለትውልዱና ለሀገራቸው እየጸለዩ እና እየባረኩ በክብር እንዲኖሩ በስፋት እየሰራች ነው ብለዋል።
ለዚህም ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለተወጣው ሰንሻይን ፊላንትሮፒ ፋውንዴሽንን እያመሰገንኩ አስተዳደራችን ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ከሚወጡ ባለሀብቶች ጋር በትብብር ለመሥራት ሁልጊዜም በሩ ክፍት ነው ሲሉም ገልጸዋል።