የሀገር ውስጥ ዜና

መልካም አብነቶች በማስፋት ወደ ብልጽግና የሚደረገውን ጉዞ እናፋጥናለን – ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

By sosina alemayehu

January 20, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በክልሉ ያሉትን መልካም አብነቶች በማስፋት የቤተሰብና ማህበራዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ወደ ብልጽግና የሚደረገውን ጉዞ እናፋጥናለን አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን የሚገኘውን ደንቢ ኢኮ ሎጅ በይፋ መመረቃቸው ይታወቃል።

ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በኢኮ ሎጁ ምርቃ መርሐ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የመደመር መንግሥት ባለፉት ዓመታት የዜጎችን ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራትን አከናውኗል።

በዚህም ኢትዮጵያ በብዙ መለኪያዎች በዓለም ደረጃ ስሟ በመልካም ገጽታ ከፍ ብሎ እንዲጠራ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ከድህነትና ኋላቀርነት ወጥተን ያለንን የተፈጥሮ ጸጋ እና የሰው አቅም በአግባቡ ለልማት በማዋል የዜጎችን ህይወት ለመቀየር እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ አጠቃላይ ዕድገት ለማምጣት በስፋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የጠራ የሃሳብ ልዕልና እንዲሁም ሃሳቡን በተጨባጭ ወደ ተግባር የሚቀይር የአመራር ስርዓት በመዘርጋቱ ሰፊውን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ትላልቅ መሰረተ ልማቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት እየበቁ መሆኑን አንስተዋል።

ክልሉ ከለውጡ በፊት የመንግሥትን የልማት እይታ ተነፍጎ መቆየቱን አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት የናፈቀውን ልማት ማጣጣም ጀምሯል ነው ያሉት።

የተደበቁ የተፈጥሮ እና ማህበራዊ ሃብቶች ወደ አደባባይ እየወጡ የኢኮኖሚና የቱሪዝም አቅም እየሆኑ እንደሚገኙም ጠቅሰው፤ የሃላላ፣ የጨበራ ዝሆን ዳና ኢኮ ሎጆች እንዲሁም የደንቢ ኢኮ ሎጅ እና የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ የልማት ፕሮጀክቶችን በአብነት አንስተዋል።

ቀደምት የነበረው የደንቢ ኃይል ማመንጫ በተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎቱ ሲቋረጥ ሃይቁ እና በአካባቢው የነበሩ መሰረተ ልማቶች ያለምንም አገልግሎት ሲባክኑ እንደነበር አስታውሰዋል።

የደምቢ ኢኮ ሎጅን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ የተፈጥሮ ሃብቶች የአካባቢው ማህበረሰብ ጭምር አሻራው እንዲያሳርፍ በማድረግ እንዲለማ በማድረግ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እና አመራራቸው ምስጋና አቅርበዋል።

የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ ፍትሃዊነት እና አካታችነትን ማረጋገጥ በመሆኑ የአርብቶ አደር አካባቢ የትምህርት ተደራሽነትን ለማሳደግ በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የበጀት ድጋፍ ለክልሉ መደረጉንም ገልጸዋል።

በክልሉ የሚገኘው የጉራ ፈርዳ ወረዳ ኩጃ ቀበሌ ሞዴል መንደር ለአቅመ ደካሞች ዘመናዊ የገጠር ኑሮን እንዲያጣጥሙ ያስቻለ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

በሶስና አለማየሁ