ቢዝነስ

ሚድሮክ በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች አሻራውን እያሳረፈ ነው – አቶ ጀማል አህመድ

By Mikias Ayele

January 20, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጀማል አህመድ ኩባንያው በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች አሻራውን እያሳረፈ ነው አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን የሚገኘውን ደንቢ ኢኮ ሎጅ በይፋ መርቀዋል።

አቶ ጀማል አህመድ በመርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ አዎንታዊ ለውጦችን ያመጡ በርካታ ፖሊሲዎች ተግባራዊ መደረጋቸውን አንስተዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ አንዱ በሆነው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተረስተው የነበሩ እንደ ማዕድን እና ቱሪዝም ያሉ ዘርፎች የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ምሰሶ እንዲሆኑ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም እንዲጠናክር ተግባራዊ የተደረጉት የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የሌማት ትሩፋት እና የገበታ ፕሮጀክቶች አስደናቂ ውጤት እያመጡ ነው ብለዋል።

ከገበታ ፕሮጄክቶች አንዱ የሆነው ገበታ ለሸገር አዲስ አበባ የኢንቨስትመንት ብቻ ሳይሆን የቱሪስቶች መዳረሻ እንድትሆን አስችሏታል ነው ያሉት።

ገበታ ለሸገር ወደ ገበታ ለሀገር ተቀይሮ ኢትዮጵያውያን የማያውቋቸውን የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲያውቁ በማድረግ መንግሥት ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በርካታ ፕሮጀክቶች እውን ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በተመሳሳይ በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ድብቅ የሆኑ የኢትዮጵያ ፀጋዎችን አካታች በሆነ መልኩ በሁሉም ክልሎች እንዲለሙ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

ከገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነውን የደንቢ ኢኮ ሎጅን ለመገንባት ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከመንግሥት ጋር በመተባበር ግንባታውን እንዲያስፈፅም ተልዕኮ ተሰጥቶት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ኩባንያቸው የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት በመወጣት ፕሮጀክቱን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

በሚኪያስ አየለ