አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገችው በሚገኘው 2ኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተገኙ ውጤቶችን በዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ላይ አቅርባለች፡፡
በገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሲዴ የተመራ ከፍተኛ የፋይናንስ ልዑክ በስዊዘርላንድ ዳቮስ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ዓመታዊ ስብስባ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡
ሚኒስትሩ ‘የአፍሪካ የስራ አንቀሳቃሽ ሞተር’ በሚል መሪ ሀሳብ በዛሬው ዕለት በተካሄደው የከፍተኛ የፋይናንስ ኃላፊዎች ስብሳባ ላይ አድርገዋል፡፡
አቶ አህመድ ሺዴ ባደረጉት ንግግር÷ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ለአህጉሪቱ ወጣቶች አካታች የስራ እድል የመፍጠር አቅም እንዳለው አብራርተዋል፡፡
በነፃ የንግድ ቀጣናው የተዘጋጁ ማዕቀፎች የስራ እድል ፈጠራን ለማስፋፋት፣ ቀጣናዊ የእሴት ሰንሰለቶችን ለማጠናከር እንዲሁም ወጣቶችንና ሴት ሥራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አስገንዝበዋል፡፡
ሁለተኛው የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በግብርና መር የምግብ እሴት ሰንሰለት፣ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት እንዲሁም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታና በከተማ ልማት ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም ሚኒስትሩ በትናንተናው እለት ‘አዲሱ ዓለም አቀፍ የጤና መዋቅር ጅማሮ’ በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡
በንግግራቸውም ፍትሃዊ፣ ተገማችና በሀገራት የሚመራ ዓለምአቀፍ የጤና ፋይናንስ ስርዓት እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል።
ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ስኬታማ ተሞክሮዎች የጠቀሱ ሲሆን፣ በተለይም በዘላቂ የልማት ግቦች አፈጻጸም ፈንድ፣ በጋራ የፋይናንስ ትብብርና በመድኃኒት ምርት ላይ የተደረጉ የኢንቨስትመንት ሥራዎችን አንስተዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለ’ሉሳካ አጀንዳ’ እና ‘አንድ ዕቅድ፣ አንድ በጀት፣ አንድ ሪፖርት’ ለሚለው መርህ ቁርጠኛ መሆኗን አንስተው፥ በዓለምአቀፍ የጤና ስርዓት ላይ ፍትሐዊነት፣ ትብብርና የጋራ ኃላፊነት ሊሰፍን እንደሚገባ አፅዕኖት ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልዑክ በ2026ቱ የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ላይ የተለያዩ የባለብዙ ወገንና የሁለትዮሽ ውይይቶችን በማድረግ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና በጤናው ዘርፍ ያሉ ችግሮች የጋራ አቋም እንዲያዘባቸው እያደረገ እንደሚገኝ የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
በሚኪያስ አየለ