አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሩሲያ ባለፉት ዓመታት በብሪክስ ውስጥ የተሰሩ ስራዎች የቡድኑ አባል ሀገራትን ግንኙነት እንዲጠናከር አስችሏል አለች።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ የብሪክስ ሊቀመንበር የሆነችው ብራዚል ባለፉት ዓመታት በተለይም በ2025 ከዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ አንጻር ለቡድኑ ውጤታማ ስራ መስራቷን አውስተዋል።
በዚህም የተሰሩት ስራዎች በብሪክስ አባል ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከሩን ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ለሦስተኛው የሩስያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ዝግጅት መጠናቀቁንም ጠቁመዋል።
የሩሲያ-ቻይና የባህል ዓመት በስኬት መጠናቀቁንና በሁለቱም ሀገራ የተለያዩ መርሐ ግብሮች መዘጋጀታቸውን አንስተው÷ የፈረንጆቹ 2026 እስከ 2027 የሩሲያ እና የቻይና የትምህርት ዓመት ተብለው መሰየማቸውን የሁለቱም ሀገራት መሪዎች ይፋ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
በሁለቱ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ትብብር ስኬቶች መመዝገባቸውንም ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ሩሲያ ከህንድ ጋር ያላትን ስትራቴጂያዊ አጋርነት ያነሱት ሚኒስትሩ÷ ፕሬዚዳንት ፑቲን ባለፈው ዓመት ታሕሣሥ ወር ላይ ከፕሬዚዳንት ድሮፓዲ ሙርሙ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር መገናኘታቸውን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም ሩስያ ከኢራን ጋር በንግድ ብቻ ሳይሆን በኢንቨስትመንትም ጥሩ እቅድ እንዳላት መግለፃቸውን ቲቪ ብሪክስ ዘግቧል።
በዚህም የቡሽህር የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በሩሲያ፣ አዘርባጃን እና ኢራን መካከል ባለው ዓለም አቀፍ የሰሜን-ደቡብ ትራንስፖርት ኮሪደር ውስጥ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
በሶስና አለማየሁ