አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥምረት ለሴቶች ድምፅ ያሰባሰባቸውን አጀንዳዎች በዛሬው ዕለት ተረክቧል፡፡
በርክክቡ ወቅት የተገኙት ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርአያ (ፕ/ር) ሀገራዊ ምክክሩ የደረሰበት ደረጃና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ በንቃት መሳተፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥምረቱ ድጋፉን ሊቀጥል እንደሚባም በመድረኩ ተነስቷል፡፡
ጥምረቱ ያስረከባቸው አጀንዳዎች በመጀመሪያ ዙር ያልተካተቱትን ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ጋምቤላ እና አማራ ክልሎችን ያሳተፈ መሆኑን የጥምረቱ የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ አድርገዋል፡፡
13 አጀንዳዎችና አራት ምክረ ሀሳቦች የተካተቱበት የአጀንዳ ሰነድ የሴቶችን የምክክር ተሳትፎና ውክልና የሚያዳብር እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ኮሚሽኑ አጀንዳዎቹን በቅርቡ ለሚከናወነው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በግብአትነት እንደሚጠቀማቸውም ተመላክቷል፡፡
መሥፍን አርአያ (ፕ/ር) የሴቶች አጀንዳዎችን ላጠናቀሩት የጥምረቱ አመራሮች በኮሚሽኑ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡